Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሆርሙዝ ሰርጥ የተቀበሩ ፈንጂዎችን አጽድተናል – ፕሬዚዳንት ትራምፕ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን መንግሥት በሆርሙዝ ሰርጥ የቀበራቸውን ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ አጽድተናል አሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ።

በዓለም ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባለው የሆርሙዝ ሰርጥ ዙሪያ እንደ አዲስ ውጥረት መንገሡ ተሰምቷል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ባካሄደችው ፈጣን ዘመቻ፣ ዓለም አቀፍ የውኃ ክልል በሆነው የሆርሙዝ መተላለፊያ ውስጥ ተቀብረው የነበሩትን ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ ማስወገዳቸውን እና ማምከናቸውን ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል የፀረ-መርከብ ፈንጂዎችን አጽድቶ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

አክለውም አሜሪካ ከዚህ በኋላ ማንኛውንም ዓይነት የጥንቃቄ ርምጃ ተግባራዊ እንደምታደርግ ገልጸው፣ “በቀጣይ አዳዲስ ፈንጂዎችን በባሕር ውስጥ ለማጥመድ የሚሞክር ማንኛውም መርከብ ወይም አነስተኛ ጀልባ ላይ ፈጣን ርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል የኢራን እስላማዊ ዘብ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መሐመድ ረዛ አሬፍ ሀገራቸው በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ያላት ቁጥጥር “ሕጋዊ እና ሉዓላዊ መብታችንን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ሀብታችንን የመጠበቅ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

“የሆርሙዝ ሰርጥ የኢራን ንብረት ነው” ሲሉ የገለጹት ባለሥልጣኑ፣ ቴህራን ማንኛውንም ዓይነት ውጫዊ ጫና ለመቋቋም ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

አሜሪካ በዛሬው ዕለት በኢራን የነዳጅ ዘይት እና የፋይናንስ መረብ ላይ ያነጣጠረ እጅግ ጠንካራ የተባለ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ያስተላለፈች ሲሆን፣ ማዕቀቡ ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸውን ሀገራት ሁሉ ዒላማ ያደረገ መሆኑን አልጃዚራ ዘግቧል።

በዚህም ምክንያት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጂኦፖለቲካዊ ፍጥጫ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አሜሪካና ኢራን ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገቡ 178 ቀናት ተቆጥረዋል።

በቴዎድሮስ ሳሕለ

Exit mobile version