አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታከናውናቸው ተግባራት ለአፍሪካ ሀገራት አርዓያ ሆናለች አሉ የአህጉር አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች፡፡
በአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ የግብርና እና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዋና ፕሮግራም ባለሙያ ክሌመንት አድጆርሎሎ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ሥርዓታቸውን ለማጠናከርና ፍላጎታቸውን በራስ አቅም ለማሟላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል።
በአህጉሪቱ እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት በራስ አቅም ለማሟላትና ጠንካራ የምግብ ሥርዓትን ለመገንባት ከኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የንግድ ሥርዓትንና አጠቃላይ የግብርና ዘርፍ የእሴት ሰንሰለቱን ማጠናከር እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
በምግብ ራስን ለመቻልና ምርታማነትን ለማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያከናወነቻቸውን ተግባራት እና ያስመዘገበቻቸውን ውጤቶች ሌሎች ሀገራት ሊጋሩት እንደሚገባም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ስንዴን በስፋት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማሟላት በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ የሀገር ውስጥ የግብርና ምርትን ማሳደግ ያለውን አስተዋጽኦ ያመላክታል ብለዋል።
ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የግብርና እና የምግብ ሥርዓትን ከአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚያስችል ተግባርን በማስተሳሰር የሚደረግ ውጤታማ ተግባር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግና ለአህጉር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአጀንዳ 2063 የቀጣናዊ ስትራቴጂክ ትንተናና እውቀት ድጋፍ ሰጪ ስርዓት ዲፓርትመንት ኃላፊ ፖል ጉቲጋ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር ለቀጣናው ሀገራት ትምህርት የሚሆን ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማጠናከርና የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ ያከናወነቻቸው ውጤታማ ተግባራት የአፍሪካ ሀገራት ሊወስዷቸው የሚገቡ ተሞክሮዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አስደናቂ እንደሆኑም አንስተዋል፡፡

