Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለመዲናችን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በቅንነትና በታማኝነት እየሰራን እንገኛለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመዲናችን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በቅንነትና በታማኝነት እየሰራን እንገኛለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ ተርሚናሎችና ገበያ ማዕከላት (በጎተራ፥ ቦሌ፣ የካ እና ቀበና) መርቀው በዛሬው ዕለት አገልግሎት አስጀምረዋል።
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እነዚህ መሰረተ ልማቶች የትራፊክ መጨናነቅን የሚያቃልሉ፣ የትራንስፖርት ሥርዓትን የሚያሻሽሉ፣ ህዝባችንን ከዝናብና ፀሐይ እንግልት የሚከላከሉ፣ በርካታ የስራ እድሎችን የሚፈጥሩ ምቹ፣ ንፁህ እና የሰውን ክብር የሚመጥኑ የዘመነ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
መሰረተ ልማቶቹ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲ እና የአውቶቡስ ተርሚናሎች፣ የአየር ብክለትን የሚከላከሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያዎች፣ ሰፊ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የንግድ ሱቆች፣ ካፍቴሪያና ሬስቶራንቶች፣ የልጆች መጫወቻና ማረፊያ ስፍራዎች፣ ምቹ የተሳፋሪ መጠበቂያ ስፍራዎች፣ የአስተዳደር እና የትኬት መቁረጫ ቴክኖሎጂዎች፣ አሳንሰሮች እና ንፁህ መፀዳጃ ቤቶች እንዲሁም የደህንነትና የአደጋ ቅድመ መከላከል ሥርዓቶች የተሟሉላቸው የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎትን ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት 3 ሺህ ብቻ የነበረውን የአንድ ጊዜ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅም እና ምንም ያልነበረንን ተርሚናል በአሁኑ ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የተገነቡ፣ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና ተርሚናሎችን ከ170 ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ለከተማችን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በተጨባጭ ቃላችንን በተግባር ስራዎችን እየፈጸምን በቅንነትና በታማኝነት እየሰራን እንገኛለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አዲስ አበባ ከዚህ በላይ ይገባታል ቀጣይም ከሰራነው በላይ እንተጋለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ እውን እንዲሆኑ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ አካላት ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
Exit mobile version