Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲሱ የዲጂታል ዘመን ሥልጣኔ በኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት፣ መታወቂያ ለማደስ ወይም የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ይደርስ የነበረው እንግልት የብዙዎቻችን የዕለት ተዕለት ትዝታ ነበር።
ረጅም ሰልፍ፣ «ዛሬ ኃላፊው የሉም» የሚል ምላሽ እና የፋይል ተፈልጎ አለመገኘት የህብረተሰቡ የዘወትር ምሬት ነበሩ። ዛሬ ግን ያ ታሪክ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ ይገኛል።
በመደመር ፍልስፍና የታነጸው የመንግሥት አካሄድ ሀገሪቱን ወደ አዲሱ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ርዕይ ሰንቆ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025»ን አጠናቅቆ ወደ «ዲጂታል 2030» ተሸጋግሯል።
ይህ ጉዞ የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን፤ የህዝቡን የአስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘይቤ የለወጠ፣ የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን የጠበቀ እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዘርፎች ላይ የታሪክ እጥፋት ማምጣት የቻለ ታላቅ ንቅናቄ ነው።
የመደመር ፍልስፍና ዋና ማዕከል ሰው እና እውቀት በመሆናቸው፤ የተበታተኑ ሀብቶችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና የዜጎችን አቅም አስተባብሮ ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የዚሁ አዲስ ዘመን መንገድ ሆኗል።
ዛሬ ላይ ያለ ጥሬ ገንዘብ የሚከናወን ግብይት እንደ ቴሌብር እና ሞባይል ባንኪንግ ያሉ ዲጂታል የክፍያ አማራጮች አሰራሩን መሰረታዊ በሆነ መንገድ ቀይረውታል።
ከትንሹ የጉሊት ነጋዴ ጀምሮ እስከ ግዙፍ የንግድ ተቋማት ድረስ ያለውን የክፍያ ሥርዓት በመቀየሩ፤ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብይቶችን በሴኮንዶች ውስጥ መፈጸም ችለዋል።
ሀገራዊ የባዮሜትሪክ መታወቂያ የዲጂታል ማህበረሰብ ግንባታ ዋና መሰረት በመሆን የዜጎችን ማንነት በፍጥነት በማረጋገጥ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ዘርግቷል።
ከፓስፖርት ቀጠሮ እስከ ንግድ ፈቃድ እድሳት ያሉ በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች በበይነመረብ የሚከናወኑ በመሆናቸው ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ የእንግልት አቤቱታዎችን በከፍተኛ ደረጃ አስቀርተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊነትን እና የተገልጋዩን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የገባው መሶብ የአንድ ማዕከል ትልቅ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ዜጎች በፍጥነት፣ በብቃት እና በአንድ ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስቻለ ዘመናዊ የህዝብ አገልግሎት ማዕከል ነው።
በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ መሰረት ዛሬ ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ100 በላይ የመሶብ አንድ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በፌዴራል መሶብ አንድ ማዕከል ውስጥ ብቻ 23 ተቋማት ተጣምረው ከ180 በላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር ይሰጣሉ።
ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም የደንበኞች እርካታ 98 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱ ተረጋግጧል። ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ እና ትውልድ ተሻጋሪ ለውጥ መምጣቱን ያመላክታል።
የመደመር መንግሥት የጣለው ይህ የዲጂታል መሰረት፤ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ማዕከላት አንዷ የማድረግ ህልሟን እውን እያደረገው ይገኛል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ የሩቅ ህልም መሆኑ ቀርቶ በየዕለቱ የምንኖረው እውነታ እየሆነ መጥቷል። ገና መስራት እና ማሻሻል የሚገቡን በርካታ ነገሮች ቢኖሩም፣ አሁን የተጣለው ጠንካራ መሰረት ግን ሀገሪቱን ወደ ተሻለች፣ የዘመነች እና የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚያሸጋግር ፈጣን መንገድ ነው፡፡
ግን ደግሞ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ የመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ይጠይቃል። ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም፣ አዳዲስ አሰራሮችን መልመድ እና አቅማችንን በዲጂታል እውቀት ማዳበር የዘመኑ ግዴታ ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ ለዲጂታሉ ዓለም የሚያበረክተው አነስተኛ አስተዋጽኦ ተደማምሮ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ያደርጋልና።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version