Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ ማሸነፍ ውስጥ እነማን ተሸነፉ?

ኢትዮጵያ በእርግጥም አሸንፋለች። የሚነሳው ጥያቄ ግን “ማንን ነው ያሸነፈችው?” የሚለው ነው። እስኪ እንጠይቅ እውነትም እነማን ተሸነፉ?
በኢትዮጵያ ያለመነጋገር ሽንቁር ለዘመናት አዋግቶናል። ያለፉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ምስጢር ሲገለፅ አለመነጋገር፣ አለመደማመጥ፣ አለመግባባት የተሰኙ ስንጥቃት አሉ። እነዚህ ስንጥቃቶች ከጠረጴዛ ይልቅ ዱር ቤቴ አስብለው መሳሪያ አስወልውለውናል።
ወንድም ከወንድሙ “ውረድ እንውረድ” ተባብሎ ደም ተፋሷል። ዓለም ኢትዮጵያን ጥንታዊት ግን ባለመግባባት የምትጋጭ አድርጎ አውቋታል። ይህ የፈጠረልን ዳፋ ድህነት፣ ርሃብና ችግር ተሳፍተው ከኛ ጋር እንዲዘልቁ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በመምከሯ ይሄንን ያለመነጋገር ጥቁር መጋረጃ ከላይዋ ላይ አንስታለች። ወንድም የወንድሙን ሀሳብ ማዳመጥ፣ ሕመሙን መስማት፣ በጋራ ሀገር የጋራ መግባባትን የሚያስቀጥሉ ጅምሮች መሰረት ተጥሏል። ተሸናፊው ግጭት፣ ደም መፋሰስና ሀሳብ ዐልቦ ፖለቲካ ናቸው።
በጋራ ያሸነፍነው ግን ይሄንን ብቻ አይደለም። ምክክር ስንጀምር “አይሆንም አይደረግም” ያሉ ኃይሎች ከውጭም ከውስጥም ነበሩ።
በአንድ በኩል “ካላቦካነው ለራት አይበቃም” ያሉ ግትር ፖለቲከኞች፣ ከግጭት እንጂ ከውይይት አናተርፍም ያሉ አኩራፊዎች ለስላቅ ተዘጋጅተው ነበር።
በኋላ ግን እኒህ አኩራፊ የሀገር ልጆች በአጀንዳዎቹ ላይ ተከራካሪም ተመካካሪም ሆነው ተገኙ፤ የኛ የሚሉት ሀሳብ እንዲደመጥ አስተጋቡት። በዚህ መሃል ኢትዮጵያ አሸነፈች።
“ኢትዮጵያውያን መመካከር አይሆንላቸው” ብለው ለስልቂያ፣ ግጭት ካለም በወንድማማቾች ፀብ ሊያተርፉ የተዘጋጁም ነበሩ። እነሱ በኢትዮጵያ ግጭት መክበር፣ እጃቸውን አስረዝመው ማትረፍን ያሰሉ ነበሩ። ይህ ስሌታቸው ግን ስሁት እንደሆነ ተረዱት።
ኢትዮጵያውያን በእርግጥም መነጋጋር መወያየት ችለው አሳዩ። በወንድማማቾች መሃል ግጭት ጠምቀው በደም ሊያሰክሩ ለነበሩ የውጭ እጅ ሰደዶች ሃፍረትን ሰጧቸው።
የኢትዮጵያ ድል ግን ይሄ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ገድበው “አይቻልምን” አሸንፈዋል፡፡
በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን በጋራ ተክለው፣ አለመተባበርን ድል በመንሳት ለመላው ዓለም አርአያ ሆነዋል፡፡
“ምርጫ ማካሄድ አይችሉም” ያሏቸውንና የዛቱባቸውንም አሸንፈው ስኬታማ ምርጫን ማካሄድ ችለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ደጋግመው ተፈትነው ደጋግመው አሸንፈዋል፡፡
በእርግጥም ኢትዮጵያ አሸንፋለች!
በአፈወርቅ እያዩ
Exit mobile version