አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ጥንካሬ የሚለካው ከሌሎች ሀገራት ጋር የምታደርገውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት በማጠናከር ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ እና የዜጎቿን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስትችል ነው።
ታዋቂው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ሊቅ ሄንሪ ኪሲንጀር “Diplomacy” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት÷ “ውጤታማ ዲፕሎማሲ ማለት የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ሳይዋጉ፣ ነገር ግን በድርድር፣ በስትራቴጂካዊ ትስስር እና በጽናት ማስጠበቅ መቻል ነው።”
ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት ዓመታት የተጓዘችበት የዲፕሎማሲ መስመር ይህንኑ የብሔራዊ ጥቅም ዘብነት በተግባር ያሳየ ነበር።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረችበትና የራሷ የዲፕሎማሲ ባህል ያላት ሀገር ብትሆንም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ያጋጠሟትን በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ወደ ስልታዊ ድል በመለወጥ ረገድ የገዘፈ ስኬት አስመዝግባለች።
ከዚህ አንጻር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የስትራቴጂካዊ ጽናት ዲፕሎማሲን ማንሳት ይቻላል።
ጆሴፍ ናይ “Soft Power: The Means to Success in World Politics” በተሰኘው መጽሐፋቸው የዲፕሎማሲ አቅም የሚገነባው ሀገራት ሀብታቸውን በባለቤትነት የመጠቀም መብታቸውን እና ፍላጎታቸውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው መንገድ ማስረዳት ሲችሉ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በዚህ እሳቤ የኢትዮጵያ መንግሥት ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እውን ለማድረግ ያደረገው ጥረት የዚህ ትልቅ ማሳያ ነው። ግብጽ እና አጋሮቿ ግድቡ እንዳይገነባ ያላደረጉት ጫና ባይኖርም፣ ኢትዮጵያ በፅናት እና በበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ጫናዎቹን በማከሸፍ ግድቡን ለውጤት አብቅታለች።
ይህም የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ከጨለማ የመውጣት መብቷን ያስከበረችበት ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ክስተት ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተደማጭነት ለማሳደግ የወሰደቻቸው ስልታዊ ርምጃዎች የዲፕሎማሲውን ስኬት ከፍ ያደረጉ ናቸው።
የሀገሪቱን የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካ ተሰሚነት በባለብዙ-ወገን ዓለም አቀፍ ድርድር ውስጥ ከፍ ያደረጋት የብሪክስ አባልነቷ እዚህ ጋር ይነሳል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አማካኝነት ችግሮችን በውስጥ አቅም የመፍታት ችሎታዋን ያሳየችበት፣ የሰላም ግንባታና የመልሶ ማቋቋም የገንዘብ ድጋፎችን ለማስገኘት መንገድ የተከፈተበት ሒደት መሆኑም አይዘነጋም።
የዲፕሎማሲው ስራ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሳብ ያደረገ ነው።
ለምሳሌ አዲስ አበባ አሁን እያስተናገደች ያለውን የ76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጨምሮ፣ የዓለም ያለ ረሃብ ጉባዔ፣ 46ኛውን የካፍ መደበኛ ጉባዔ፣ 9ኛውን የአፍሪካ ንግድ መድረክ እና በርካታ ታላላቅ መድረኮችን አስተናግዳለች።
ከፊት ለፊት ደግሞ 32ኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ32) ለማስተናገድ የተመረጠችው የአረንጓዴ ዐሻራ ዲፕሎማሲዋ ያመጣው ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል።
እንዲሁም በኢኮኖሚው እና በደህንነቱ ዘርፍ የተሰሩ በርካታ ሥራዎች ሀገሪቱን ከዓለም ጋር አጣብቀው አስተሳስረዋታል።
በዓለም ንግድ ድርጅት ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክ እና አርጀንቲና ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ተደራሽነት ስምምነቶች ተደርገዋል። ከቻይና ጋር የ330 ሚሊየን ዶላር የቡና፣ የቅባት እህሎች እና ማዕድናት ኤክስፖርት ስምምነት ተፈራርማለች።
ከዩናይትድ ስቴትስ ፔንታጎን ጋር ስትራቴጂካዊ የመከላከያ ስምምነት እንዲሁም ከቻይና፣ ብራዚል እና አልጄሪያ ጋር የፍትሕ እና የሕግ ትብብሮች መመስረት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
በሳይንስ እና ቴክኖሎጂው ዘርፍም ከሩሲያ ጋር የኒውክሌር ልማት ፕሮጀክት፣ ከላይቤሪያ ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ቴክኖሎጂ፣ ከእንግሊዝ ጋር ደግሞ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ስምምነቶችንም ተፈራርማለች።
ከዚህ ውጪ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲውም የዜጎችን በዓለም አቀፍ መድረክ መብታቸው እና ጥቅማቸው እንዲከበር የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።
ጋሬዝ ኢቫንስ “The Responsibility to Protect” በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የሀገርን የፖለቲካ ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር የዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅን ቅድሚያ ይሰጣል ይላሉ።
ባለፉት አምስት ዓመታት በችግር ላይ የነበሩ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች በክብር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገበት መንገድ የመንግሥትን ለዜጎች ቅድሚያ የመስጠት ተግባርን ያሳያል።
ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ከኳታር እና ዮርዳኖስ ጋር በተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሰራተኞች መብትና ጥቅም እንዲጠበቅ በመደረጉ በ2014 ዓ.ም 40 ሺህ ገደማ የነበረው ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በ2017 ዓ.ም ወደ 503 ሺህ ከፍ ማለት ችሏል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑት እነዚህ አጠቃላይ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር፣ ተደማጭነቷን በማሳደግ እና የዜጎቿን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ዘመን ማሳለፏን ሕያው ምስክር ናቸው።
በታሪኩ ለገሰ

