አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለማችን ላይ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት መዛባት ቀደም ሲል ይነገሩ እንደነበሩት የወደፊት ስጋቶች ሳይሆን፣ በአሁኑ ወቅት የበርካታ ሀገራትን ህልውና እየፈተነ ያለ ተጨባጭ አደጋ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ፓነል የሚያወጣቸው ጥናቶች እንደሚያመለክቱት÷ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ እና የአየር ሁኔታ መዛባት በተለይም በታዳጊ ሀገራት ዘላቂ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የምግብ ዋስትና ማጣት እና ከፍተኛ የሕዝብ መፈናቀል እያስከተሉ ይገኛሉ።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሰረተ ልማቶች ሲወድሙና የምርት ዘርፎች ሲመናመኑ፣ ሀገራዊ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ይሸረሸራል፤ ይህም ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አዳጋች ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፋዊ ፈተና እና የውስጥ ስጋት ቀድማ በመረዳት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን የልማት ፖሊሲዎቿ ማዕከል አድርጋ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች።
ለዘመናት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀውን የግብርና ዘርፍ ከአየር ንብረት ተጽዕኖ ነፃ ማድረግ እና የአካባቢ ጥበቃን ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ማስተሳሰር የዚሁ ስትራቴጂ አካል ነው።
በኢትዮጵያ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ በግልጽ እንደተመላከተው÷ የኢኮኖሚ ብዝኃነት እና የአካባቢ ደህንነት ሳይነጣጠሉ የሚሄዱ የልማት ማዕቀፎች ናቸው። ሀገሪቱ በካርበን ልቀት ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ዕድገትን በመተው፣ ሙሉ በሙሉ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት በአፍሪካ ደረጃ አቅኚ ያደርጋታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የውሃ፣ የነፋስ፣ የፀሐይ እና የባዮ ጋዝ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ የኃይል ፍላጎት ከመሙላት ባሻገር የካርቦን ልቀትን በከፍተኛ ደረጃ የመቀነስ ሚና አላቸው።
በታዳሽ ኃይል የሚመረት የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ መቻሏ፣ የቀጣናውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር እና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከቀላል የዛፍ ተከላ መርሐ ግብር አልፎ የኢኮኖሚ እና የአካባቢ ጥበቃ መሳሪያ ሆኖ ይገኛል። የተራቆቱ ተፋሰሶችን መልሶ ማገገም፣ የአፈር ለምነትን መጨመር እና የከርሰ ምድር ውሃን ማጎልበት ማስቻሉ ለግብርናው ዘርፍ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
በፕሮግራሙ የታቀፉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች የተራቆቱ መሬቶችን ከመሸፈን ባሻገር የአርሶ አደሩን ገቢ አሳድገዋል። ጥራት ያላቸው የፍራፍሬ ምርቶች ለአውሮፓ እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ገበያዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸው የግብርና ወጪ ንግዱን አበዝቶታል።
የደን ሽፋንን በማሳደግ ከዓለም አቀፍ የካርበን ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችሉ ተቋማዊ እና ሕጋዊ ማዕቀፎች መጠናከራቸው ሀገሪቱ ከአካባቢ ጥበቃ በቀጥታ የፋይናንስ ጥቅም እንድታገኝ እያደረገ ነው።
የመስኖ መስፋፋት፣ የበጋ ስንዴ ልማት እና ድርቅን የሚቋቋሙ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ማዳረስ የግብርናውን ዘርፍ በዝናብ ላይ ብቻ የነበረውን ጥገኝነት በመቀነስ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን ውጥን እውን እያደረጉት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሒደት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት የመከላከል እና የተከሰተውን ሁኔታ የመላመድ አቅምን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው።
ይህ አካሄድ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ተላቃ፣ ዘላቂና የማይበገር የኢኮኖሚ መዋቅር እንድትገነባ የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ ነው።
በታሪኩ ለገሰ

