አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሮጀክቶች በጊዜያቸዉ ሲጠናቀቁ ትርፋቸዉ ከገንዘብ ያልፋል፡፡
ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ሲቀር የሚታጣው ከገንዘብ ባሻገር ሊገመቱ የማይችሉ ብዙ ሀብቶችን ነው፡፡
ለአብነትም የመንገድ ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ ንግድን ፣ጤናን፣እንቅስቃሴን ያውካል፤ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች መዘግየት ከአርሶ አደሮች ባለፈ ምርትን የሀገርን የምግብ ዋስትና መንገድ ይጎዳል፤ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ቢሆኑ ማህበረሰቡን የሚጎዱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ፕሮጀክቶች በተመደበላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው የሚወስደው ተጨማሪ ገንዘብ ሌሎች የጤና ፣የትምህርት እና ሌሎች መሰረታዊ ፕሮጀክቶች እንዳይሰሩ ማነቆ በመሆን የማህበረሰብ ፍላጎቶች እንዳይሟሉ ያደርጋል፡፡
ታዲያ የመደመር መንግሥት ይህን ችግር በሚገባ ሊያስተካክሉ የሚሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም ረጅም ጊዜዎች የፈጁ በርካታ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቋል ፤ ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ግድቡ ከተመደበለት በጀት እና ጊዜ በእጅጉ የዘገየ ነበር ፤ የመደመር መንግሥትም ይህን ለማስተካከልና ግድቡን ለማጠናቀቅ የወቅቱን የውጭ ምንዛሬ ጫና በመቋቋም ስራው እንዲቀጥል በማድረግ ግድቡን ለሕዳሴው አብቅቶታል።
በተመሳሳይ የአንድ ወጣት እድሜን ያክል 18 ዓመታትን የቆየዉ የመገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክትም ጊዜን ፣ገንዘብን እና ተጠቃሚነትን ከበሉ ፕሮጀክቶች መካከል የሚነሳ ነው ፡፡
ነገር ግን የፕሮጀክት መጓተት ይበቃል ያለው የመደመር መንግሥት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት በፍጥነት እና በጥራት እንዲከወን በማድረጉ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ሊጠናቀቅ የቀረው 6 ከመቶ ያክል ስራ ብቻ ሆኗል፡፡
እንደ ፣ጎርጎራ እና ሌሎችም የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች እንዲሁም የከተማና የገጠር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ደግሞ ከታቀደላቸዉ ባነሰ ጊዜ አልያም በታቀደላቸዉ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ የስኬት ማሳያዎች ናቸው፡፡
የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን የሚጀምር ብቻ ሳይሆን በፍጥነት እና በጥራት የሚጨርስ ፤ ቃልን በተግባር የሚቀይር መንግሥት መሆኑን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ አረጋግጧል፤ እያረጋገጠም ነው።
በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት የጀመራቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጠረ ጊዜ የመጨረስ እና አዳዲሶችን የመጀመር ተግባር ኢትዮጵያ የልማት ስራዎችዋን በፍጥነት ማከናወን የምትችል ሀገር መሆንዋን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የሚያሳዩ ምስክሮች ናቸው፡፡
በእመቤት ሲሳይ

