አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሚያደርሰውን ግፍና መከራ ለማስቀረት ሕዝቡ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል አሉ የሥምረት ፓርቲ የምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ ጠዓመ ዓረዶም።
አቶ ጠዓመ እንደገለጹት፥ ቡድኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመናድ፣ ከጽንፈኞች እንዲሁም ከሻዕቢያና ግብጽ ጋር በመጣመር የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማናጋት ትንኮሳ እያደረገ ይገኛል።
ሕገ-ወጡ ቡድን ከፍተኛ የዝርፊያና የሃብት ማሸሽ ተግባር ላይ የተሰማራ፣ በወጣቶች ላይ አፈናና እስር የሚያካሂድ የዘራፊዎች ስብስብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተቃራኒው የትግራይ ህዝብ ወጣቶችና ዳያስፖራው በቤተ-እምነቶችና በመገናኛ ብዙሃን የቡድኑን እኩይ ሴራ አምርረው እየኮነኑ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት ህዝቡን ከጉስቁልና ለመታደግ ያሳየው ትዕግስት የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጠዓመ፤ በቀጣይም የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ፓርቲያቸው የቡድኑን ሴራ የማጋለጥ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የትግራይ ህዝብና ወጣቶች የጀመሩትን ተቃውሞ በማቀጣጠል የጥፋት ቡድኑን ህልም እንዲያከሽፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

