አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር መተኪያ የሌላት፣ የማንነትና የነጻነት መገለጫ ናት። ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ የገጠሟቸውን ሀገራዊና ውጫዊ ፈተናዎች አልፈው ታሪካቸውንና ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው ቆይተዋል።
በታሪክ ሂደት ውስጥ የሀገሪቱን የልማትና የጂኦ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለማስተጓጎል ከሚሞክሩ ውጫዊ ኃይሎች መካከል የግብፅ አቋም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።
በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ እና ግብፅ ግንኙነት በዲፕሎማሲ፣ በሃይማኖት እና በውሃ ፖለቲካ የተቃኘ ቢሆንም፤ ግብፅ የሀገራቱ ግንኙነት በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አበክራ ሰርታለች።
ሐጋይ ኤርሊክ (ፕ/ር) “Ethiopia and the Middle East” በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለውን ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ትስስር የሚወስን ዋና ምክንያት የአባይ ወንዝ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይሁን እንጂ ግብፅ የአባይ ወንዝ መነሻው ከኢትዮጵያ መሆኑን ሆን ብላ በመዘንጋቷ እና ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትጠቀም በቅኝ ግዛት ውል በማሰር ለበርካታ ዓመታት ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጓ፣ የሀገራቱን ግንኙነት በተለያየ ጊዜ እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።
በተለይም በ1959 ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያን ያገለለ የሁለትዮሽ የውሃ ክፍፍል ስምምነት መፈራረማቸው፣ ግብፅ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ እንዳትጠቀም ጽኑ ፍላጎት እንዳላት በግልፅ ያሳያል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ስትጀምር መሠረታዊ ዓላማዋ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የሕዝቧን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እና ቀጣናዊ ትስስርን መፍጠር መሆኑን ግልፅ ብታደርግም፤ ግብፅ ለዘመናት በኢፍትሃዊነት ለብቻዋ ስትጠቀምበት የቆየውን የውሃ መብት አስከብራ ለማስቀረት ባላት ፍላጎት የተነሳ፣ የግድቡን ግንባታ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ለመቃወም ሞክራለች።
ይሁን እና ኢትዮጵያ ለግብፅ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ሳትንበረከክ መብቷን አስከብራ የህዳሴውን ግድብ ጨርሳ ለአገልግሎት አብቅታለች።
ነገር ግን ሁሌም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የማትፈልገውና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን የማትሻው ግብፅ፣ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላም አርፋ አልተኛችም። ራሷን እንደተበዳይ በመቁጠር ኢትዮጵያን በዓለም ፊት ለማሳጣት መጣሯን ቀጥላለች፤ አለፍ ሲልም የተለያዩ ዛቻዎችን፣ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን፤ እንዲሁም በውስጥ ጉዳይ ላይ እሳት በመለኮስ የውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ትሰራለች።
የሕዳሴውን ግድብ እውን ከመሆን ማቆም ያልቻለችው ግብፅ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለማኮላሸት የማትፈነቅለው ድንጋይና የማትገባበት የዓለም መድረክ የለም።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ካላት ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ስፋት አንፃር፣ ቀጣይነት ያለው የባሕር በር እና የወደብ አማራጭ ማግኘት ለደህንነቷና ለልማቷ ወሳኝ ጉዳይ ነው። የባሕር በር ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነትና መብት ሳይነካ፣ በሰላማዊ መንገድ፣ በንግድና በስምምነቶች ላይ ተመስርቶ ሊተገበር የሚገባው መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች፤ የባሕር በር ፍላጎቷም የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ እና ለቀጣናው ሰላም አምጪ በሆነ መንገድ ነው እየሰራች ያለችው።
የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሰላም እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ አቅም ቢሆንም፣ ግብፅ ግን ይህንን ባለመሻት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት ለመግታት የቀጣናውን ሀገራት ጭምር በተንኮል እየቀረበች የኢትዮጵያን መውጫ በር ለመዝጋት እየሞከረች ነው።
ይሁን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፡ “ኢትዮጵያን ማንም አቁሟት አያውቅም፤ ማንም አያቆማትም። ይህ የማይሆን ዝም ብሎ ባዶ ፍላጎት ነው፤ ኢትዮጵያ የሌሎችን መብት ሳትነካ ሕዝቦቿን ይዛ ብሔራዊ ጥቅሟንና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ከምትሄደው መንገድ የሚያስቆማት አንዳች ኃይል አይኖርም።”
በቤተልሔም ግርማ

