Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምሥራቅ አፍሪካ በውሃ ምርመራና ምርምር የልሕቀት ማዕከል ለመሆን እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምሥራቅ አፍሪካ በውሃ ምርመራና ምርምር የልሕቀት ማዕከል ለመሆን በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው አለ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት።

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሀብት ጥራትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል ስፔሻላይዝድ ላቦራቶሪ አስመርቋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የውሃ ሃብት ጥራትን ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በዛሬው ዕለት ያስመረቀው ላቦራቶሪ ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነትና ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ላቦራቶሪው የውሃ ጥናት፣ ምርምር እና የልማት ሥራዎችን በማዘመን የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት እንደሚያሻሽልም አስረድተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታመነ ኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በዘርፉ የምርምር ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ላቦራቶሪው ተቋሙ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምክርና በቴክኒክ አገልግሎት የተሰጠውን ተልዕኮ በተሻለ አቅምና ጥራት እንዲወጣ የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለዘረፉ ዘመኑን የዋጀ፣ ብቁ፣ ተግባራዊ ክህሎት ያለውና ችግር ፈቺ የሰው ሃይል ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

ዘመናዊ የውሃ ጥራት ላቦራቶሪው በምሥራቅ አፍሪካ በውሃ ምርመራና ምርምር የልሕቀት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ መገንባቱን ነው የገለጹት፡፡

ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቅሰው ÷ እቅዱን ለማሳካት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ላቦራቶሪው በውሃ ዘርፍ የሚከናወኑ ምርምሮችንና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለማካሄድ ያስችላል ያሉት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የስፔሻላይዝድ ላቦራቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አብዱርሃማን ሰይድ ናቸው።

የትኛውንም ዓይነት የውሃ ናሙና ምርመራ በሀገር ውስጥ አቅም በማከናወን ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚያስችል መጠቆማቸውንም የተቋሙ መረጃ አመልክቷል፡፡

ተቋሙ ከስፔሻላይዝድ ላቦራቶሪ ሕንጻው በተጨማሪ የስፖርት ሜዳ፣ የመዝናኛ ሥፍራ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መርቆ ሥራ አስጀምሯል፡፡

Exit mobile version