አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት የታሪክ ጉዞ በሀገር ሉዓላዊነት፣ በነጻነት እና በተጋድሎ ጽናት ላይ የተገነባ የብዙ ዘመናት ቅርስ ነው።
ይህ ሰራዊት የሀገርን ድንበር እና ግዛታዊ አንድነት ከመጠበቅ ባሻገር፣ በችግርና በፈተና ወቅት ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ፤ የሀገር ሕልውና አለኝታ በመሆን ዘመናትን ተሻግሯል።
ከዚህ ባለፈም ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር የከፈለውን ዋጋ እና ያሳየውን የላቀ የሙያ ሥነ -ምግባር ታሪክ በወርቅ ቀለም መዝግቦታል፤ ጉዞው የጀግንነት፣ የጽናት እና የሀገር ፍቅር ተረክ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ መሠረቱ የነጻነት ተጋድሎ ነው፤ በ1888 ዓ.ም በዓድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ መሠረት፣ መላው ሕዝብ በተነሳሽነት እና በጽናት የሕዝብ ሰራዊት ሆኖ ተሰለፈ።
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ወረራ በመመከትም የዓድዋን ድል አበሰረ። ይህ ድል የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስከበሩ ባለፈ፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እና የኩራት ምልክት ሆኖ አልፏል።
ሰራዊቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከባሕላዊ የሕዝብ ሰራዊትነት ወደ ዘመናዊ እና ፕሮፌሽናል ኃይልነት መሸጋገሩ ይታወቃል፡፡
እንደ ሐረር ጦር አካዳሚ ባሉ የሥልጠና ተቋማት የታነፀው ይህ ኃይል፣ በ1928 ዓ.ም የጣሊያን ሁለተኛ ወረራ ወቅት ከዓርበኞች ተጋድሎ ጋር በመቀናጀት የመቋቋም አቅሙን እና ለሀገር መስዋዕት የመሆን ባሕሉን አጠናክሯል።
በዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ወረራ በተቃጣ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት እና የሀገርን ጥሪ ተቀብሎ በነቂስ የወጣው መላው ህዝብ ያሳዩት ጀግንነት ታሪካዊ ነበር። የአምባገነኑን የዚያድ ባሬ ጦር በማሸነፍ የካራማራን ድል ያበሰሩበት፣ የሀገሪቱን ክብር እና ግዛታዊ አንድነት በጽናት ያስከበሩበት የማይረሳ ምዕራፍ ሆኖም ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ወሰን ከመጠበቅ አልፎ የዓለም ሰላም ዘብም ሆኖ በችግር ጊዜ በመገኘት በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በሶማሊያ እና በሱዳን (አብዬ) በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ ያሳየው የላቀ የሙያ ሥነ ምግባር፣ ጀግንነት እና የሕዝብ ወገንተኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አክብሮትን አትርፎለታል።
በአሁኑ ጊዜም፤ በመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊትን አቅም፣ ዝግጁነትና ፕሮፌሽናሊዝም ለማሳደግ የዘመናዊነት እና መዋቅራዊ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል።
ሰራዊቱ ከማንኛውም ፖለቲካዊና ወገናዊ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት በፅናት እንዲጠብቅ የሚያስችሉ የህግ፣ የአሰራርና የመዋቅር ማሻሻያዎች ተደርገዋል።
በተጨማሪም የሰራዊቱን ወታደራዊ ስልጠናና ትምህርት በዘመናዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ ማበልፀግ፣ የወታደራዊ ታክቲክና የሳይበር ደህንነት አቅምን ማጎልበት እንዲሁም የሎጂስቲክስና ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ማስታጠቅ ዋና ዋና የተከናወኑ ተግባራት ናቸው።
በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ መሻሻያዎችም ሰራዊቱ የደህንነት አደጋ ስጋትንም ሆነ ሀገርን ከጠላት የመጠበቅ አቅሙን ጽኑ መሰረት ላይ በመጣል፤ የተሟላ ቁመና ላይ ሆኖ በተጠንቀቅ ቆሞ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትናንት እስከ ዛሬ የሀገርን ሕልውና እና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የማይተካ ሚና የተጫወተ የነጻነት ባለታሪክና የጀግንነት መገለጫ ነው።
ከትውልድ ወደ ትውልድ በተሸጋገረው የፅናትና የሀገር ፍቅር እሴት ላይ በመመስረት፣ አሁንም በዘመናዊ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ብቃት በመገንባት የሀገር ሰላም፣ የሕዝብ ደህንነት እና የአንድነት ዋስትና ሆኖ ይቀጥላል።
በመልካም ፈቃዱ

