አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት የሀገራችንን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ገንብተዋል አሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዡ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊዎች ሀገራዊ የጋራ የፀጥታ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡
የፀጥታ ኃይሉ ከውስጥና ከውጭ በሽብርተኞች እና በፅንፈኛ ቡድኖች የተጠነሰሱ በርካታ ሴራዎችን በማክሸፍ ኢትዮጵያ የማትበገር ሀገር መሆኗን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ በዘረጋው ቅንጅታዊ አሠራር ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ ማድረጉን አንስተዋል።
በቀጣይ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአዲስ ዓመት፣ የመስቀል እና የእሬቻ በዓላት እንዲሁም የመንግሥት ምስረታ ሁነቶችም በስኬት እንዲጠናቀቁ ግልፅ የሆነ ስትራቴጂካዊ እቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ማንሠራራት የማይፈልጉ ባንዳዎችና ባዳዎች የሕዝቡን አንድነት ለመሸርሸር የሐሰት መረጃዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት የሀገርን ገጽታ ለማበላሸት ቢጥሩም የፀጥታ ኃይሉ ሕዝቡን በማሳተፍ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

