Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የቱሪዝም ዘርፉ ገቢ እንዲጨምር አስችሏል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የቱሪስቶችን ፍሰት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉን የገቢ ምንጭነት እያሳደጉት መጥተዋል አለ የክልሉ ደንና የዱር እንስሳት ድርጅት።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አራርሳ ረጋሳ እንዳሉት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የደን ሀብትን በማልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ትኩረት ከመስጠት ባሻገር የቱሪዝም መስህብና የሀብት ምንጭ ማድረግ ተችሏል።

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የደን ሽፋን በማደጉ የዱር እንስሳት ደህንነት እንዲጠበቅና ሸሽተው የነበሩም እንዲመለሱ ብሎም ይበልጥ እንዲበራከቱ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም የዱር እንስሳትና ብርቅዬ አእዋፋት ጭምር ሁነኛ የጎብኝዎች መስህብ እየሆኑ በመምጣታቸው አበረታች ገቢ እየተገኘ ነው ብለዋል።

የዘርፉ ልማት የሥነ ምህዳር መታደስን ከመፍጠሩ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ትኩረት መሳብ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በክልሉ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮችን ተፈጥሮአዊ ሀብት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ሕጋዊ የአደን ስፍራዎችን በመለየት የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

በእርጅና ላይ የሚገኙና ጉዳት የደረሰባቸውን የዱር እንስሳት በመለየትም እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version