አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የሐዋላ እና ፈቃድ የሌላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ ህብረተሰቡ፣ የዳያስፖራ አባላት እና ደንበኞች ፈቃድ የሌላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ወኪሎች እና ሕገ ወጥ የሐዋላ መረቦችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
እነዚህ ሕገ ወጥ ተግባራት በኢትዮጵያ ሕግ በጥብቅ የተከለከሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በእነዚህ መንገዶች ገንዘብ መላክም ሆነ መቀበል ደንበኞችን ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ፣ ለክፍያ መዘግየት፣ ለባንክ ሒሳብ ዕገዳ፣ እንዲሁም ለሕግ ተጠያቂነት እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የገንዘብ ዝውውር እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ ዜጎች ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውን የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶችን ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡
ሕገ ወጥ መንገዶችን መጠቀም ላኪዎችንም ሆነ ተቀባይ ቤተሰቦችን አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ለአስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ነው የገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ያልተሰጣቸውን 17 ሕገ ወጥ አስተላላፊ ድርጅቶችን ይፋ አድርጓል።
በዚህም አዱሊስ መኒ ትራንስፈር፣ አማል ኤክስፕረስ፣ አማል ዩኤስኤ፣ አማና ኤክስፕረስ፣ አቫንቲ፣ አዋሽ ዳይሬክት፣ ባካል መኒ ትራንስፈር፣ ጁባ ኤክስፕረስ፣ ራስሚ ፔይ፣ ረማድ ፔይ (ወይም ረማዳ ፔይ ካህ)፣ ሽጌይ መኒ ትራንስፈር፣ ታጅ ፋይናንሻል ሰርቪስ፣ ታሳ ፔይ፣ ተወከል መኒ ሰርቪሰስ፣ ዩኤስዋየር፣ ወርልድ ዳይሬክት ሊንክ እና ዞላ የተሰኙ ድርጅቶች ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው መሆናቸው ገልጿል።
ህብረተሰቡ ገንዘቡን ለመጠበቅ እና የላከው ገንዘብ በፍጥነት መድረሱን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸውን የሐዋላ ድርጅቶች ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ህብረተሰቡ ገንዘብ ከመላኩ በፊት የመረጠው አቅራቢያ በብሔራዊ ባንክ ይፋዊ የተፈቀደላቸው ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ መካተቱን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል።

