አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
አቶ አረጋ ከበደ በዚህ ወቅት÷ ክልሉ የገጠሙትን ፈተናዎች ተሻግሮ በኢኮኖሚ እና በልዩ ልዩ የልማት መስኮች ተወዳዳሪ እንዲሆን በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በሰው ሃብት ልማት፣ በተቋም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ልማት፣ ሠላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ በኩል የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።
የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት እና የ5 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን ለመተግበር የተደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ የተቋማት፣ የአመራሩና የባለሙያው የመፈጸም አቅም ማደግ ለሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል።
የጋራ ግንዛቤ ለጋራ ስኬት መሠረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ከታለመው ርዕይ ለመድረስ ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

