አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ለሀገር፣ ለማሕበረሰብና ለግለሰብ ያላቸው ዘላቂ ፋይዳ በገንዘብ ተምነን የምናልፈው ብቻ አይደለም፡፡
የክረምት ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ትስስር፣ የአንድነትና የመተጋገዝ ተምሳሌት ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዚሁ አብሮነት ትልቁ ማሳያ ሆኖ በማህበረሰቡ ውስጥ ስር እየሰደደ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ከሰኔ 2018 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም ማብቂያ ድረስ በተለያዩ ዘርፎች በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 9 ቢሊየን 467 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ስራን ለማከናወን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፤ ውጤቱም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እየታየ ይገኛል፡፡
በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ላይ ዜጎች የዘመመ ጎጇቸው ይቃናል፤ የጎደለ ማጀታቸውን ይሞላል፤ የተራቆተ ገላቸውም ይለብሳል፡፡
ታዲያ ይህ ተግባር ይዞት የሚመጣው የሕሊና እርካታ በገንዘብ ብቻ የሚመዘን አይደለም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ለሚሳተፉ ወጣቶች የሕይወት ክህሎትን፣ የመሪነት ብቃትንና የዜግነት ኃላፊነት ስሜትን ያጎናጽፋቸዋል። አዕምሯዊ እርካታን ከመስጠቱ በላይ የወጣትነት ጉልበትና እውቀትን ለበጎ አላማ በማዋል አወንታዊ ስብዕናን ይገነባል።
ወደ ማሕበረሰቡ ስንመጣ ደግሞ፣ የአቅመ ደካሞችንና የአነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እንግልት በመቀነስ ረገድ ወደር የለውም።
የመጠለያ፣ የጤና፣ የትምህርትና የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመጋራት የማህበራዊ ፍትህና የመተጋገዝ ባህልን በጽኑ መሰረት ላይ ይተክላል።
በሀገር ደረጃ ሲታይም መንግሥት ለልማት የሚያወጣውን ከፍተኛ በጀት በመቆጠብ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ ይደግፋል፤ የወጣቱን ኃይል ለልማትና ለሰላም ግንባታ በማሰለፍም የሀገርን አንድነት ያጠናክራል።
ዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታላላቅ ሀገራዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በቢሊየኖች የሚቆጠር የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የጉልበት አስተዋፅኦ በተደረገበት የቤት እድሳት መርሐ ግብር፣ የብዙ ሺህ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ያረጁ ቤቶች ታድሰዋል፤ አዳዲስ ቤቶችም እየተገነቡ ነው፤ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁም አሉ።
በጎ አድራጎትን በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ብንመለከተው በአቅም ማነስ ምክንያት ሕክምናቸውን መከታተል ያልቻሉ ዜጎችን በነጻ ሕክምና በማድረግ ጤናቸውን እየመለሰ ይገኛል፡፡
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎች ሕክምና ለመስጠትም እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳም በወሊድ ጊዜ ደም አጥታ የምትሞትን እናት ቁጥር ለመቀነስ እየተሰራ ነው፡፡
ከትምህርት ጋር ሲታይም አዳዲስ ት/ቤቶች ተገንብተዋል፤ ከደጋፊዎችና ከበጎ ፈቃደኞች በተሰበሰበ ቁሳቁስና በጀት ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ለሚዘጋጁ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተማሪዎች ደብተር፣ ዩኒፎርምና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የበጎ ፈቃድ አግልግሎት የወቅታዊ ድጋፍ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ግንባታ ዋና መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

