Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

“መስጠት መቀበል ነው” የበጎ ፍቃድ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰው በመሆን ውስጥ ትልቁ ውበት ለሌሎች መኖርና የሌሎችን የሕይወት ሸክም ማቅለል መቻል ነው።
በጎ ፍቃደኝነት ማለት ክፍያ ወይም ማንኛውንም ዓይነት የግል ጥቅም ሳይሹ፤ በራስ ሙሉ ፍላጎትና ተነሳሽነት ጊዜን፣ እውቀትን፣ ጉልበትንና ገንዘብን ሌሎችን ለማገዝ እንዲሁም ለማህበረሰብ እድገት ማዋል ነው።
የበጎ ፍቃድ ሥራ የሕብረተሰብ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የሰዎችን ችግር የሚቀርፍና ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በጎ ተግባር ነው።
ይህ በጎ ተግባር የሚሰጠው ጥቅም ለተቀባዩ ብቻ ሳይሆን ለሰጪውም በዋጋ የማይተመን የሕሊና ምንዳ ትርፍ አለው።
በማህበረሰብ ደረጃ በኢኮኖሚ ወይም ማህበራዊ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችን ከመደገፉም በላይ እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተሳሰብ ፍቅርን ያጠናክራል።
በኢትዮጵያ የክረምት ወቅት ዝናብና ቅዝቃዜ የሚበዛበት ቢሆንም ለሀገራችን ወጣቶችና ማህበረሰብ ግን የፍቅር፣ የደግነትና የትብብር ትልቅ መድረክ ይከፍታል።
በተለይም ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት በእነዚህ ወራት በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በበጎ ፍቃደኝነት ይሰማራሉ።
የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተራ የበጎ አድራጎት ሥራ ባለፈ የማህበረሰብን ሕይወት የሚቀይር፣ ወጣቶችን የሚያንፅና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ትልቅ ንቅናቄ ሆኗል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በጎ ፍቃደኞች በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና ተፈጥሮን በመጠበቅ የኢትጵያን ትልም ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተጨማሪም በዝናብ ወቅት የሚቸገሩ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችንና አቅም የሌላቸውን ወገኖች ቤቶች በማደስና በመገንባት ከክረምቱ ቅዝቃዜና እንግልት ይታደጋሉ።
ተማሪዎች በክረምት ወቅት እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ነፃ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብ ሌላው ዋና ተግባር ነው።
የሰውን ሕይወት ለማዳን የሚደረግ የደም ልገሳ ንቅናቄና ስለ ጤና አጠባበቅ ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራዎች በስፋት ይከናወናሉ።
እነዚህ የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴዎች ወጣቶች ጊዜያቸውን ካልተገቡ ተግባራትና አላስፈላጊ ውሎዎች በመጠበቅ፤ ኃላፊነትን፣ ችግር ፈቺነትንና ማህበራዊ ግንኙነትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።
በተጨማሪም በመንግሥት ሊሸፈኑ የማይችሉ በርካታ ማህበራዊ ክፍተቶችን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በነፃ የሰው ኃይል በመሸፈን የኢኮኖሚ ጫናን ይቀንሳል፤ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርንም በማጠናከር መከባበርንና አብሮነትን ይገነባል።
በአጠቃላይ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት “መስጠት መቀበል ነው” የሚለውን ድንቅ እሴት የሚያንጸባርቅ ነው።
ወጣቶች ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ለወገናቸው ሲሰጡ፣ በምላሹ ደግሞ የወደፊት ሀገር ተረካቢነታቸውን የሚያረጋግጥ መልካም ስብዕናና ልምድ ያገኛሉ።
ለበጎ ፍቃደኝነት የሚያስፈልገው ሀብት ወይም ገንዘብ ሳይሆን ሰዎችን ለመርዳት የሚያነሳሳ ቀና አስተሳሰብና ለበጎነት ክፍት የሆነ ልብ ብቻ ነው።
እያንዳንዱ ሰው ባለው አቅምና እውቀት በማህበረሰቡ ውስጥ በሚደረጉ የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ አጋርነቱን ማስመስከር ይችላል።
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version