Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ።
የዋና ጠቅላይ መምሪያው ከፍተኛ አመራሮች በአማራ ክልል የፍትህ ተቋማትን የሪፎርም አተገባበር ጎብኝተዋል።
ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በፍትህ ተቋማት ዘመኑን የዋጁ አስደናቂ የሪፎርም ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተተገበረው በዲጂታል የተደገፈ የኢ-ፋይል አሰራር ፍትሃዊ፣ ግልጽና የተገልጋዩን እንግልት መቀነስ ያስቻለ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ባሉበት ሆነው በበይነ መረብ በመከታተል አስተማማኝ ፍትህ እንዲያገኙ መደረጉ የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የተሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያም ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠርና የዲጂታላይዜሽን አሰራርን እውን በማድረግ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የዳበረ የፍትህ ስርዓት ለማስፈን በተሰራው ስራ ትልቅ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በጉብኝቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አመራሮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
Exit mobile version