አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው የትብብር ማዕቀፍ ጋር የሚተሳሰር ነው አሉ የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት እንዳሉት፤ የባሕር ወደቦች ለአንድ ሀገር ንግድና ኢንቨስትመንት እጅግ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ጎረቤት ሀገራት በአግባቡ ሊረዱት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የባሕር በር የማግኘት ሂደቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ጥቅምና ዕድገትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው የትብብር ማዕቀፍ ጋር የሚተሳሰር መሆኑንም ነው ያነሱት።
በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ድምፃቸውና ፍላጎታቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ በጋራና በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ አፍሪካ ለዚህ ትብብር ዋነኛዋ ድምጽ ሆና እየወጣች ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን አፍሪካን ከእስያ ጋር በማስተሳሰር ረገድ መግቢያ በር ሆና እያገለገለች እንደምትገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትብብርንና በሕግ ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስጠበቅ ተመሳሳይ አመለካከት ባላቸው ሀገራት መካከል የበለጠ ወዳጅነትና አንድነት እንዲኖርም ጥሪ አቅርበዋል።

