አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁለተኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በዚህም ምሽት 12 ሰዓት 30 ላይ ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ኢፕስዊች ታውንን ያስተናግዳል።
በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በሃል ሲቲ ሽንፈት የገጠመው ማንቼስተር ዩናይትድ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባል።
ማንቼስተር ዩናይትድ ከዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሰው ሃል ሲቲ መሸነፉን ተከትሎ የቡድኑ ብቃት ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።
በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመሩት ቀያይ ሰይጣኖቹ በቀጣይ ጨዋታዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይጠበቃል።
በ2025/26 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ስር መሻሻሎችን ማሳየቱ ይታወሳል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በ2025/26 የውድድር ዓመት በካሪክ ስር ያሳየውን መሻሻል በዚህኛው የውድድር ዓመት ይበልጥ እንዲያሳድገውም በደጋፊዎች ዘንድ ይጠበቃል።
በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አንድሬይ ሳንቶስ፣ ካርሎስ ባሌባ እና ዮሪ ቴሊማንስን በማስፈረም የመሐል ክፍሉን አማራጭ ያሰፋው ቡድኑ በቀጣይ እነዚህን ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር በማዋሀድ ይዞት የሚቀርበው የጨዋታ መንገድ ተጠባቂ ነው።
ከ9 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሰው ሃል ሲቲ በመጀመሪያ ሳምንት የተሸነፈው ዩናይትድ ዛሬ ምሽት በሜዳው ኦልድትራፎርድ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል።
ተጋጣሚው ኢፕስዊች ታውን በበኩሉ በሊጉ ተከታታይ ድሉን ከማሳካት ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።
ኢፕስዊች ታውን በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ሰንደርላንድን ማሸነፉ ይታወሳል።
በማንቼስተር ዩናይትድ በኩል አማድ ዲያሎ እና አዲሱ ፈራሚ ካርሎስ ባሌባ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ቀን 10 ሰዓት ላይ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ብራይተንን ያስተናግዳል።
በአሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ እየተመራ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ቼልሲ የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታ ድል ማድረጉ አይዘነጋም።
ከአውሮፓ መድረክ ውድድሮች ውጪ የሆነው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በሊጉ የሚያደርገው ፉክክር ይጠበቃል።
ተጋጣሚው ብራይተን በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ድል ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች ተከታታይ ድላቸውን ለማሳካት ወደ ሜዳ የሚገቡ ይሆናል።
በተመሳሳይ ቀን 10 ሰዓት ላይ ሊድስ ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ እንዲሁም ሰንደርላንድ ከፉልሃም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሊጉ ጨዋታ ነገ ሲቀጥል ምሽት 4 ሰዓት ላይ አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ከአርሰናል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።
አርሰናል በሊጉ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት አስቶንቪላ ደግሞ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።
የጨዋታ ውጤት ግምታችሁን አጋሩን።
በወንድማገኝ ጸጋዬ

