አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በሀገራዊ ማንሰራራት ውስጥ የአዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ እንተጋለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀጣይ አምስት ዓመትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በየደረጃው ባሉ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ውይይት እየተደረገበት ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ህዝባችን የሰጠንን ኃላፊነት መነሻ ያደረገ ስትራቴጂክ እቅድ ነድፈን ቃላችንን በተግባር ቆጥረን ፈጽመን የከተማችን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም ከተማችን ደግሞ ተወዳዳሪ እንድትሆን አድርገናል።
ሕዝባችን ያለፈውን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በሚገባ በመፈጸማችን ለቀጣዩ አምስት ዓመታት በድጋሚ እንድናገለግል ድምጹን ሰጥቶናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ከተማዋን ተወዳዳሪ ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች ነዋሪው እምነት ጥሎ ዳግም ኃላፊነት እንደሰጣቸው አብራርተዋል።
የዛሬው የመድረክ ውይይትም ነዋሪው የጣለውን እምነት እና የሰጠውን ኃላፊነት መነሻ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት እና በ2019 በጀት ዓመት በእቅድ ዝርዝር ግቦች ላይ ተወያይቶ በማዳበር የባለፉትን አምስት ዓመታት አፈጻጸም በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጁነት የሚረጋገጥበት መድረክ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም 24/7 የመፈጸም ባህልን ይበልጥ በማሳደግ፣ አመራሩ ከፊት ሆኖ የበለጠ በመሮጥ፣ ህዝቡንና የልማት አጋሮችን በማስተባበር እንዲሁም በማስተባርና ተሞክሮዎችን በማስፋት፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሚካሄደው ሀገራዊ ማንሰራራት ውስጥ የአዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌትነት ለማረጋገጥ እንደሚተጋ ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
መድረኩ በክረምት ወቅት ከተያዙት የ90 ቀን ስራዎች ውስጥ የ60 ቀናት አፈጻጸም ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

