Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመግባባት ዴሞክራሲን እውን ያደረገው የመደመር መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ልዩነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። የሐሳብ፣ የፖለቲካና የጥቅም ልዩነቶችም በራሳቸው ችግር አይደሉም።
ትልቁ ጉዳይ ግን እነዚህን ልዩነቶች እንዴት እናስተናግዳለን? የሚለው ነው።
ልዩነትን በግጭትና በዜሮ ድምር ፖለቲካ ማስተናገድ መከፋፈልን ያባብሳላል፤ በውይይት፣ በመደማመጥና በምክክር ማስተናገድ ግን ልዩነቶችን ወደ የጋራ አቅም ይቀይራል። ይህም የመግባባት ዴሞክራሲ ዋና መርህ ነው።
መግባባት ተኮር ዴሞክራሲ ማለት ሁሉም አንድ ዓይነት እንዲያስብ ማድረግ አይደለም።የተለያዩ ሐሳቦች በነጻነት እንዲገለጹ፣ ድምጾች እንዲደመጡና ከልዩነቶች መካከል የጋራ መፍትሔ እንዲፈለግ ማድረግ ነው።
በዚህም ከመነጠል ወደ መደመር የሚያሸጋግር የፖለቲካ ባህል ይፈጠራል። በዚህ ረገድ በቅርቡ የተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር ጉልህ ምዕራፍ ነው።
የተለያዩ ሐሳቦችን ወደ አንድ ሀገራዊ ጠረጴዛ በማምጣት ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ መምህራን፣ ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብና የፖለቲካ ተዋናዮች ጨምሮ ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የምክክሩ ትልቁ ትርጉም መናገር ብቻ ሳይሆን መደማመጥ፣ የሌላውን እይታ መረዳትና ከልዩነቶች መካከል የጋራ መፍትሔ መፈለግ ነው። ይህም ከኢትዮጵያዊው የሽምግልናና የመደማመጥ ባህል ጋር የሚገናኝ እሴት ነው።
የሀገራዊ ምክክሩ መጠናቀቅ አንድ ትልቅ ምዕራፍ ሲሆን፤ የምክክርና የመግባባት መንፈስን ወደ ዕለታዊ የፖለቲካ ሕይወት ማስረጽ ግን ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው።
ዘላቂ ውጤቱም በሰነዶች ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ባህላችንና በማኅበራዊ ግንኙነታችን ላይ በሚፈጥረው ለውጥ ይለካል።
በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version