Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለሰላም ያልተዘጋው በር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውና የማንኛውም እድገት መሠረት ሰላም ነው።

ሰላም ለአንድ ግለሰብ፣ ማህበረሰብም ሆነ ሀገር የቆመችበት ጠንካራ መሠረት ነው። ሰላም ሲታወክ የመኖር ህልውና ይናጋል፤ ሀገርም ወደ መፍረስ አደጋ ታኮበኩባለች።

ለዚህ ነው በየትኛውም መመዘኛና መስፈርት የሰላም አማራጭ ሁልጊዜም ቢሆን አዋጭና የማይተካ የሚሆነው። የሰላምን አማራጭ መገፋት ለራስም፣ ለወገንም ሆነ ለሀገር አለማሰብ ከመሆኑም በላይ ጤነኝነቱንም አጠራጣሪ ያደርገዋል። በአጭሩ ሰላም ለድርድር የሚቀርብ ቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ ዘላቂና ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን፣ የፀጥታ ችግሮችንም በውይይትና በምክክር ለመፍታት መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጥረቶችን አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ በተለያዩ ጊዜያት ከሰላም ጋር በተያያዘ ባደረጉት ንግግር፡ “መንግሥት ስለ ሰላም ሲል ሁልጊዜም ቢሆን አንድ ርምጃ ወደፊት በመራመድ በሩን ክፍት ያደርጋል። ሰላም የሽንፈት ሳይሆን የብልህነትና የትልቅነት ማሳያ ነው”። ሲሉ መንግስታቸው ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ግልጽ አድርገዋል።

ይህንን የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በርካታ ታጣቂዎች ከጫካ በመመለስ ጥያቄያቸውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማቅረብ በመጀመራቸውም በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም ማምጣት ተችሏል።

ይሁን እንጂ አሁንም በየጫካው የሚንቀሳቀሱና በሕዝብ መካከል ሆነው የዜጎችን ሰላምና ዕለታዊ እንቅስቃሴ የሚያደፈርሱ አካላት በመኖራቸው ሙሉና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል።

ማንኛውም ታጣቂ ኃይል “የምታገልለት ሕዝብ” በእኔ ትግል ምክንያት ሰላም አጣ፣ መውጣቱና መግባቱ ስጋት ሆነበት ብሎ ካመነ፣ የሕዝቡን የተደጋጋሚ ሰላም ጥሪ መስማት ይኖርበታል። ከሕዝብ ፍላጎት በላይ የሚሆን ምንም ዓይነት የፖለቲካ ዓላማ ሊኖር አይችልም።

ሕዝብ ሰላም ፈልጋለሁ እያለ፣ “ካንተ በላይ ስለ አንተ ሰላም እኔ አውቅልሃለሁ” የሚል አካሄድ ፍጹም ከሕዝብ ፍላጎት የራቀ ነው።

ዛሬ ላይ በሀገራችን ሰላም ባላቸው አካባቢዎች የሚካሄዱ ታላላቅ የልማት ሥራዎችን እያዩ፣ በሰላም እጦት ምክንያት የልማት አየር ያጣቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “ጠብመንጃ የያዘ አካል የያዘውን መሳሪያ አስቀምጦ ወደ ሰላም ጠረጴዛ ከመጣ፣ መንግሥት ለመደራደርም ሆነ ሀሳብን ለመቀበል ዝግጁ ነው። ምክንያቱም ከጠብመንጃ ድምፅ ይልቅ የውይይት ድምፅ ሀገርን ይገነባል” ሲሉ የሰላም በሩ ፈጽሞ እንዳልተዘጋ አረጋግጠዋል።

በመሆኑም በየጫካው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱም ሆኑ በየአካባቢው የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ካለፈው ስህተት ሊማሩ ይገባል።

ከሰላም ውጪ ሌላ የሚያሸንፍ አማራጭ የለም። የተከፈተውን የሰላም በር በመጠቀም፣ ጥያቄዎችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ዜጎችን ከስጋት ነፃ ማድረግ፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ የታሪካዊ ኃላፊነት ጥሪ ነው።

በታሪኩ ለገሰ

 

Exit mobile version