አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ አህጉር ከቀደሙት እና ጠንካራ ታሪክ ካላቸው የወታደራዊ አቪዬሽን ተቋማት አንዱ ነው።
ላለፉት ዘመናት የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ይህ ተቋም ÷ በየጊዜው ከተከሰቱ የጂኦ-ፖለቲካ እና የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር እራሱን እያደሰ አሁን ላይ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል መሠረት የተጣለው በ1920ዎቹ አጋማሽ ሲሆን ÷ በይፋዊ ደረጃ በ1930ዎቹ ተደራጅቶ ሥራ ጀምሯል።
በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በስዊድን የአቪዬሽን ድርጅቶች እገዛ የሰው ኃይል ሥልጠና በመጀመር የተለያዩ የጦር አውሮፕላኖችን የታጠቀ ዘመናዊ ኃይል መገንባት ተችሎ ነበር።
በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ከሶቪየት ኅብረት ጋር በተደረገ ወታደራዊ ትብብር ተዋጊ አውሮፕላኖችን በመታጠቅ የአህጉራችን ግዙፍ አየር ኃይል ለመሆን በቅቷል።
በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ጦርነቶች የአየር ላይ የበላይነት፣ የቴክኒክና የውጊያ ብቃቱን በሚገባ አስመስክሯል።
ይሁን እንጂ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከአስርት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የታጠቃቸው አውሮፕላኖች በየሜዳው በቁጥቋጦ ተወርሰውና ተረስተው እስከመቅረት ደርሰው ነበር፡፡
እንደ ተቋምም ቢሆን ያልተስተካከለ ቁመና ላይ ሆኖ የመበተንና የመፍረስ ጫፍ ላይ ተቃርቦ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
በመደመር መንግሥት በተካሄደው የመከላከያ ሪፎርም እና በመደመር እሳቤ መሪነት የአየር ኃይሉን አቅም መሠረታዊ በሆነ መንገድ የሚቀይሩ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን አየር ኃይል ከተለመደው የባህላዊ ጄት ውጊያ ባሻገር፣ የዘመኑን የመረጃ፣ የቅኝት እና የትክክለኛ ጥቃት ቴክኖሎጂዎች ባለቤት የሆነ የተቀናጀ የአየር መከላከያ መዋቅር ገንብቷል።
በቢሾፍቱ የሚገኘው የአየር ኃይል አካዳሚ እና የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የሥልጠና ቁሳቁስን እና ሲሙሌተሮችን እንዲታጠቅ በማድረግ የፓይለቶች፣ የኢንጂነሮችና የቴክኒሻኖች ሥልጠና ጥራት እንዲያድግ ተደርጓል።
አውሮፕላኖችን እና ሄሊኮፕተሮችን በሀገር ውስጥ የማደስ፣ የማሻሻል እና የመጠገን አቅም በመገንባቱ የውጭ ጥገኝነትንና የውጭ ምንዛሪ ወጪን በእጅጉ መቀነስ አስችሏል፡፡
በዚህም ዘመናዊዎቹ ሁለገብ ተዋጊ አውሮፕላኖች ጥገና እና ማሻሻያ ተደርጎላቸው በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ ይገኛሉ።
በሲ-130 ሄርኩለስ እና በሄሊኮፕተሮች የታገዘ ፈጣን የሎጂስቲክስ አቅም እንዲሁም ዘመናዊ የራዳርና የአየር መከላከያ ሥርአቶችንም ያካተተ ነው።
በሌላ በኩል እንደ ባይራክታር ቲቢ 2፣ ዊንግ ሎንግ 2 እና አኪንቺ ያሉ ዘመናዊ የጥቃትና የቅኝት ድሮኖችን በመታጠቅ የቅኝትና የዒላማ መቺነት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
አየር ሃይሉ ከውጪ ሀገር ከሚገቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ላይም ተደርሷል፡፡
ወታደራዊ ሙያ ብቃትን፣ የሥነ ምግባር እና የብሔራዊ አንድነት እሴቶችን የተላበሰ የሰው ኃይል በመገንባት ተቋሙ ለሀገር ሰላም፤ ደህንነትና ሉዓላዊነት አስተማማኝ አለኝታ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊ የጀግንነት ውርሱን ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የጦር አቪዬሽን ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር፣ የሀገርን ሰማይ በአስተማማኝ ሆኔታ የመጠበቅና የቀጣናውን ሰላም የማስከበር ብቃቱን በተግባር እያረጋገጠ በሙሉ ቁመና ላይ ሆኖ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።
በመልካም ፈቃዱ

