አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25 ፣ 2018 (ኤፍ ኤምሲ) የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተከተለው ስልታዊ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ወደ ላቀ ዓለም አቀፋዊ ከፍታ ማሸጋገር ችሏል፡፡
ለጎረቤት ሀገራት ትብብር ቅድሚያ የሚሰጠውን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ከቃላት ባለፈ በተግባር በመተርጎም የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ግንኙነት ከጥርጣሬ አጥር ወጥቶ ወደ ጽኑ ስልታዊ አጋርነት እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት መርህን በመከተል ፍሬ ማፍራት ችላለች፡፡
የመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለመመስረት ያለመ ነው፤ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ትስስር ማጠናከርንም ያጠቃላል፡፡
በዓለም ዲፕሎማሲያዊ መድረኮች ተፅዕኖዋ እየጎላና ጥንካሬዋ እየጎለበተ የመጣው ሀገራችን አሁንም የፓን አፍሪካኒዝም ማማና የፅናት ተምሳሌት መሆኗን በድጋሚ እያረጋገጠች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ አሁን በዓለም የምትፈለግ ሀገር ናት፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በመሰረተ ልማት ከማስተሳሰር ባለፈ በቀጣናው ሽብርተኝነትና አለመረጋጋትን በጋራ መከላከልና የሰላም አስከባሪ ኃይል የማሰማራት ስራዎችም ለቀጣናው ትስስር ተስፋ ፈንጣቂ ነው፡፡
በድንበር አካባቢ ባሉ ሕዝቦች መካከል ያለውን ባህላዊና ማህበራዊ ትስስር ማሳደግ እንዲሁም በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም መርህን የመከተል ስልቶችም የኢትዮጵያን ተቀባይነት የጨመሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ ሀገራት ጋር በቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች ጥብቅ መስተጋብሮች የተሳሰረች ናት፡፡
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የኢኮኖሚ ዋስትናዋ ናት፤ ለወጪና ገቢ ንግዷ የጂቡቲ ወደቦች ትጠቀማለች፤ ሁለቱ ሀገራት በትላልቅ አውራ መንገዶችና በባቡር መሰረተ ልማት ከተሳሰሩ ምዕተ አመት አልፏቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባላት ትሰስር በሁለቱ ሀገራት መካከል ካለው የንግድ ልውውጥ ባሻገር በፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ይሰራሉ፡፡
በፀረ ሽብርተኝነት ትብብር ኢትዮጵያ ለአመታት በአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮና በሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት የአልሸባብን የሽብር ቡድን ለመዋጋት ወታደሮቿን ሶማሊያ ውስጥ ማሰማራቷ ለጎረቤቷ ሰላም መቆሟን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ትሸማመታለች፣ ትሸጣለች፤ ትገዛለች፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሰላማዊ ጉርብትና ምሳሌ ሆኖ ሊነሳ የሚችል ነው፡፡
በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን የሚነሱ የውስጥ ግጭቶችን በኢጋድና በሁለትዮሽ ድርድር ለመፍታት ቀዳሚ ሚና ተጫውታለች፡፡
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ሳይጎዳ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በጋራ ጥቅም ላይ ማዋልና የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን አጽድቃለች፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ ተግባራት በማከናወን ቀጣናዊ መረጋጋት እንዲፈጠር አድርጋለች፤ በዚህ መንገድም የቀጣናው አብሪ ኮከብ ሆና ቀጥላለች፡፡
በትዕግስት ግዛቸው

