Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረት በመላው ዓለም ለሚገኙ ትውልደ አፍሪካውያን ፍትህ በቁርጠኝነት ይሰራል – ሞሀመድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ አፍሪካውያን ፍትህና ልማት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሀመድ አሊ ዩሱፍ፡፡
ሊቀ መንበሩ የትውልደ አፍሪካውያን ቀንን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፍሪካና የትውልደ አፍሪካውያን ታሪክ እና መጻኢ እድል ተነጣጥሎ የሚታይ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡
በአሜሪካ፣ ካሪቢያን፣ አውሮፓ እስያ እና ፓስፊክ ለሚኖሩ በ100 ሚሊየን የሚቆጠሩ ዘረ አፍሪካውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች በዓለም ዙሪያ አህጉሪቱን በማስተዋወቅ ለአፍሪካ ባህልና ልማት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህ ዕለት አፍሪካን በውጭ ከሚኖሩ ልጆቿ ጋር ለማስተሳሰር እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ታሪክ ለማውሳትና እንደ አንድ ቤተሰብ የወደፊት የአፍሪካን እጣ ፋንታ በጋራ ለመወሰን እንደሚታሰብ አንስተዋል፡፡
ህብረቱ ጥቁር ሕዝቦች እውቅና፣ ፍትሕና ልማት እንዲያገኙ እንዲሁም የመጤ ጠል እንቅስቃሴዎችንና ጥቃቶችን፣ በጥቁር ህዝቦች ላይ የሚደርሰውን መድልኦ ለመከላከል ይሰራል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አፍሪካውያን ዳያስፖራዎችን የቤተሰብ አካል አድርጎ ይቆጣራቸዋል ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ አፍሪካውያን ዳያስፖራዎች የአፍሪካ አጀንዳ 2063ትን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚኖሩ ዘረ አፍሪካውያን ሰላምና ብልፅግናን በመመኘት የአፍሪካ ህብረት ከአፍሪካውያን ዳያስፖራዎች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
Exit mobile version