የኢትዮጵያ በሰላም፣ በጋራ ተጠቃሚነት እና በሉዓላዊነት መከበር ላይ የተመሠረተ ውጫዊ ግንኙነቷ ዛሬ ላይ ከየትኛውም ጊዜ በላቀ መልኩ ተጨባጭ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ሀገራችን በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት አቋም እየተከበረ፣ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖዎቿም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ መጥተዋል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በሰላም አስከባሪነት፣ በሽብርተኝነት ትግል እንዲሁም በቀጣናዊ መረጋጋት ግንባር ቀደም ሚና የምትጫወተው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም መለያዋ የሆነውን ይህን ጽኑ የሰላም አቋም በተግባር አሳይታለች።
በአፍሪካ በፋጣን እድገት ውስጥ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ሀገራችን በተለይም እየሰፋ የመጣው የንግድ ልውውጥ መጠን እና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንዲሁም ከሀገር በሚወጡ ስትራቴጂካዊ ሸቀጦች ፍላጎት ማደግ ጋር ተያይዞ፣ የባህር በር ማግኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የንግድ ተወዳዳሪነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጥያቄም ጭምር ሆኗል።
መንግሥት ይህንን ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይት፣ በሕግ ማዕቀፍ እና በጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win) መርህ እውን ለማድረግ የያዘው ጽኑ አቋምም ሰፊ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትንና ሁለንተናዊ አጋርነትን እያጎናጸፈው ይገኛል።
ባለፉት የለውጥ አመታት የኢትዮጵያ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ሕጋዊነትና ትክክለኛነት ከዕለት ተዕለት የጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች ጋር ተጣምሮ በተግባር እየተረጋገጠ መጥቷል።
የባህር በር ተደራሽነት ለቀጠናው የንግድ ልውውጥ፣ ለሎጅስቲክስ ትስስር፣ ለኢንቨስትመንት ፍሰት እና ለጋራ የደህንነት ማዕቀፍ ያለው ወሳኝ ሚና በሰፊው በመታመኑ፣ የጋራ አጠቃቀም አማራጮች በተግባር እውን እንዲሆኑ የአጋሮች በጎ ተጽዕኖዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረዋል።
እነዚህ አዎንታዊ እውነታዎችና ሀገራችን የምታነሳቸውን ስትራቴጂካዊ ጥያቄዎች ከዲፕሎማሲያዊ ዕውቅና አልፎ ወደ መሬት ወርዶ የሚሠራበትን ዘላቂ ተግባራዊ አጋርነት በመፍጠር አስተማማኝ መሠረት እየጣሉ ነው።
ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ተደማጭነት ያረጋገጠ ታሪካዊ ድል ነው። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ እንዲሁም በቀጠናው የሰላም ግንባታ ሂደት የምታበረክተው አርአያነት ያለው አስተዋጽኦ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል።
በአጠቃላይ የሀገራችን የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ከፍታ እና የሰላምና የልማት ፍትሃዊ፣ ስትራቴጂካዊ ጥያቄዎቻችን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸው የላቀ የብልጽግና ጉዟችን እውነተኛ ማሳያ ነው። መንግሥት ሕዝባችንን እና ሀገራችንን የረጅም ጊዜ ጥቅም ለማረጋገጥ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በጥብቅ ፍላጎትና በቁርጠኝነት አጠናክሮ ይቀጥላል።
# የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

