አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ለ15 ዓመታት ያካሄደው የጋራ ጉዞ በእምነት ተቋማት ትብብርን በማጠናከር፣ ሰላምንና ማህበራዊ ውህደትን በማሳደግ ለሀገራዊ እድገትና ልማት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ 15ኛ ዓመት ምስረታ በዓል እና 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ጉባዔው የእምነት አባቶችና መሪዎች የሚሰበሰቡበት መድረክ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ታሪክ፣ የህዝቦቿን ህሊናና የጋራ መሻቶች የሚዘከርበትና የሚመከርበት ታሪካዊ መድረክ ነው።
የጉባዔው የ15 ዓመት ጉዞ የእውቀት፣ የጥበብ፣ የማስተዋልና የአብሮነት መገለጫ ሆኖ መቀጠሉን በማውሳት÷ የእምነት ተቋማት አስተምህሯቸውን፣ መንፈሳዊ ጸጋቸውንና አንድነታቸውን እንደ ሃብት በመውሰድ ለሀገር በአንድነት መቆማቸውና በጋራ መምከራቸው ለትውልድ የሚሻገር ትልቅ እሴት ነው ።
የጉባዔው መሪ ሃሳብ እምነትን በተግባር ከማጽናት፣ የሰላምን በረከት ከማስፋፋትና ለኢትዮጵያ የልማት ግስጋሴ ከማበርከት ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ የሰላም ዋጋ ለእድገትና ለልማት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በተከታታይ ትውልዶች ሐሳብ፣ ጉልበት፣ ደም፣ ላብ እና ጸሎት የተገነባች ሀገር እንደሆነች እና የእምነት ተቋማት ለዘመናት የህዝቡን ሞራልና ስብዕና በመቅረጽ የሀገሪቱ ከፍተኛ ማህበራዊ መሠረቶች ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ ነው ያሉት።
የእምነት መሪዎችና ተቋማት በተለይ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን ከአጉል ባህልና ልማድ በመጠበቅ፣ ለሀገርና ለህሊና የቆመ ትውልድ በመገንባት የላቀ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያዊ ባህል፣ ሥነ ምግባር፣ ህሊናና ጨዋነት የሚጻረሱ የጥፋት፣ የሌብነት፣ የጭካኔና ሌሎች አሉታዊ ተግባራት እንዳይስፋፉ ማስተማር፣ መገሰጽና ማረም የእምነት ተቋማት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የእምነት መሪዎች በችግርና በተስፋ መቁረጥ ወቅት የብርታት ምንጭ፣ በተከፋፈሉ ልቦች ውስጥ የመመካከር፣ የመተባበር፣ የይቅርታ እና የእርቅ አስተላላፊዎች መሆናቸውን ገልጸው÷ በእምነት ስም የሚፈጸሙ ጽንፈኛ ተግባራት የሃይማኖትን ቅዱስ ዓላማ እንደሚጻረሩ አስረድተዋል።
በቅርቡ በተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት የእምነት ተወካዮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ÷ ለሀገራዊ መግባባትና ሰላም መመለስ በተደረገው ጥረት የእምነት ተቋማት ሚና ላቅ ያለ ነበር ብለዋል።
መመካከር በእውነት፣ በይቅር ባይነትና በጋራ መግባባት ላይ እንዲጸና እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን በነጻነት እንዲያጋራ የእምነት ተቋማት ቀጣይ ሚና አስፈላጊ ነው ፤ ይህም ለዘላቂ ሰላምና ለሀገራዊ እድገት ጠንካራ መሠረት ይጥላል ነው ያሉት።
ሀገራዊ እድገትና ልማትን መደገፍ የፖለቲከኞች ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለሀገር ግንባታ የበኩሉን ሚና መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
መንግሥት የእምነት ተቋማት ለዘላቂ ሰላም፣ ለማህበራዊ ውህደትና ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በመረዳት የእምነት ተቋማትን ነጻነት በመጠበቅ ረገድ ለተቋማቱ ቀጣይ ሥራ የሚያስፈልገውን አጋርነት፣ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በዮናስ ጌትነት

