አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብጽ የውሃ አጠቃቀምና አያያዝ ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ ነው አሉ የቀድሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ቡድን አባል እና የውሃ ሀብት ተመራማሪው አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ፡፡
አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ተራራማና ጥልቅ ሸለቆዎች ውሃን ለማከማቸት እጅግ ምቹ ናቸው፡፡
ውሃን በእነዚህ ቀዝቃዛ አካባቢዎች ማከማቸት ለአባይ ተፋሰስ ሀገራት የሚጠቅም መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህንን ሁኔታ በግብጽ ከሚገኘውና በበረሃማ አካባቢ በመገንባቱ ከፍተኛ የውሃ ትነት ከሚያጋጥመው የአስዋን ግድብ ጋር በማነጻጸር አቅርበውታል።
በአስዋን ግድብ በዓመት ብቻ ከ15 እስከ 16 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚተንና እንደሚባክን አብራርተዋል፡፡
ውሃን በኢትዮጵያ ጥልቅ፣ ጠባብ ሸለቆዎች ውስጥ እና አመቺ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ማከማቸት የትነት መጠንን ለመቀነስ እንደሚያስችልም አስረድተዋል።
ዋናው የውሃ ማከማቻ በኢትዮጵያ መሆኑ በሙቀት ሊባክን የሚችለውን በርካታ መጠን ያለው ውሃ ከማዳኑም በላይ፣ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚለቀቀውን የውሃ መጠን አስተማማኝና የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2005 በግብፅ ከባድ የጎርፍ አደጋ በደረሰበት ወቅት የሀገሪቷ መሐንዲሶች ‘ዌስተርን ስፒልዌይ’ የተባለውን መስመር በመክፈት በቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ ውሃ ወደ ቱሽካ ሸለቆ አቅጣጫ እንዲቀይር ማድረጋቸውን አውስተዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ውሃ የማከማቸት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር በተፋሰሱ ላይ ያለውን ከመጠን ያለፈ የውሃ ብክነት ለመቀነስና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መሠረተ ልማቶች ለጎርፍ አደጋ እንዳይጋለጡ ለመከላከል እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ተራራማ ሸለቆዎች የሚከማቸው ውሃ መጨመር በግብፅና ሱዳን በኩል በየዓመቱ የሚባክነውን አጠቃላይ የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ ማከማቻዎች ጥቅም በውሃ ጥበቃ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፈው ንጹሕና በተመጣጣኝ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲያገኙ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
እንዲህ ዓይነት የኢነርጂ ትብብር በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ላለው የኢኮኖሚ ትብብር ተጨማሪ አቅም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከእነዚህ ሁለገብ ጥቅሞች ተጠቃሚ ለመሆን በናይል ወንዝ ላይ በጋራ ተጠቃሚነትና መተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትብብር ሊፈጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

