አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ተስፋ ይሰነቃል፤ ሰዎች ለአዳዲስ ፈተናና እድሎች ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፤ የአዲሱን ዓመት መምጣት አስታክከው ለቀጣይ የህይወታቸው ጉዞ አዳዲስ ውሳኔዎችን ይወስናሉ፡፡
በአዲሱ ዓመት የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው በመመኘት፤ የትናንቱን ስኬትና ውድቀት መርምረው፤ መንፈሳቸውን አድሰው ይቀበላሉ፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ያለፈውን አመት የህይወት ጉዞ ገምግሞ አዲስ እቅድ የማውጣት ልምምድ ውጤታማ ያደርጋል፡፡
አዲስ አመት እየመጣ እንደመሆኑ የዘመን ለውጥ በሰዎች ላይ የሚፈጥረውን ተስፋ እና ለለውጥ መነቃቃት በተመለከተ ከስነ-ልቦና አማካሪ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
የስነ ልቦና አማካሪው ታሪኩ ነጋሽ ለፋና ዲጂታል የሰጡት ሙያዊ ማብራሪያም ይህንን እውነት የሚያጠናክር ነው፡፡
በአዲስ ዘመን መዳረሻ ቀናት ሰዎች የቀደመውን አመት ያሳለፉበትን መንገድ ገምግመው አዲስ እቅድ ቢያወጡ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአዲስ አመት መዳረሻ ሰሞን የሚታዩት የተፈጥሮ ክስተቶች ሁሉ የሰውን ልጅ ተስፋ የሚያለመልሙ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የዝናቡ መገታት፤ የፀሐይዋ መገለጥና የምድሪቱ መፍካት የአዲስ ጅማሮ አመላካች በመሆቸው ለአዲስ የለውጥ ውሳኔ አነቃቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱ ቀን ለአዲስ ጅማሮ እድል የሚሰጥ ነው ያሉት የስነ ልቦና ባለሙያው፤ አዲስ አመት ደግሞ ሰዎች ያለፈውን አመት የህይወት መንገድ ገምግመው የተሻለ ማንነት ለመገንባት ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ መነቃቃት የሚያገኙበት ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አመት መዳረሻ ቀናት እየተገባደደ ባለው አመት የተከሰቱ በጎ ወይም ጥሩ ያልሆኑ ክስተቶችን መለስ ብሎ በመመልከት ለመማር ምቹ ጊዜያት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ያለፈውን አመት ጉዞ ቆም ብሎ በመቃኘት በትምህርት፣ በስራ፣ በትዳር አልያም በሌሎች የህይወት መንገዶች የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ከራስ ጋር በመማከር አዲስ ነገር ማቀድ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል ሲሉ መክረዋል፡፡
በምሕረት ደምሴ

