Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

እስከ መስከረም፤ በአዲስ ኢትዮጵያዊ ስሜት ወደ አዲሱ ምዕራፍ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአስራ ሶስት ወራት ጸጋ የተከበበችው፣ የራሷ የቀን መቁጠሪያና የተለያዩ ባህሎች ያሏት ውብ ምድር ኢትዮጵያ፣ በመስከረም ወር በአደይ አበባ አጊጣ አዲሱን ዓመት ትቀበላለች።
የዘንድሮው የዓመቱ መባቻ ግን ከየትኛውም ጊዜ በላይ በታላቅ ድምቀት የሚታወስና አዲሱን 2019 ዓ.ም ፈጽሞ የተለየ የሚያደርገው ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በታላቅ ስኬት አጠናቅቃ፣ ታሪካዊውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ፍጻሜ በማብሰር ሙሉ ሀገራዊ ድልን ተቀዳጅታለች።
በዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና፣ የተሻለ ነገዋንና የለመለመ ተስፋዋን በአዲስ ዓመት ለመቀበል በደስታ ደጃፍ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያውያንም ባስመዘገቧቸው ድሎች ሰላምን፣ ህብረትንና አንድነትን የክት ልብሳቸው ባደረጉበት በዚህ አዲስ ምዕራፍ የማይበገር አሸናፊነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።
የዚህ ታላቅ ድል ባለቤቶች እንደመሆናችን መጠን የምንቀበለው አዲስ ዓመት ከወትሮው ለየት ያለ የዕድገት፣ የብልጽግና እና የሰላም ምዕራፍን የሚከፍት ነው።
የኢትዮጵያ ሰማይ በሰላም ጸንቶ፣ የልማት ማማዎቿ ከፍ ብለው ይታያሉ፤ በግብርና፣ በንጹህ ሃይል ማመንጨት፣ በቱሪዝም እና በመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተመዘገቡ ያሉት ታላላቅ ስኬቶችም የነገዋን ብሩህ ተስፋ አብስረውናል።
የሀገራችንን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ የተተገበሩ ሀገር በቀል ስራዎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የዜጎችን ህይወት ያሻሻሉ የልማት ማዕበሎች የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋና ከፍታ ያረጋግጣሉ።
አዲሱ ዓመት የተገኘውን ድል ይበልጥ ለማጽናት፣ የተጀመሩ የኢኮኖሚ ከፍታዎችን ለማፋጠን እና የትውልዱን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚሰራበት የቁርጠኝነት ዘመን ነው።
ወደ አዲሱ ዓመት በሚወስዱን ጥቂት ቀናት ውስጥ ሀገራዊ ሰላምን ማስጠበቅ፣ በልማት ጎዳናዎች መሳተፍ እና አረንጓዴ አሻራችንን ማሳረፍ የሁላችንም ቁርጠኝነት ሊሆን ይገባል።
አሮጌውን አራግፈን፣ መጥፎውን በበጎ ተክተን፣ በአዲስ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ፍቅር አዲሱን ዓመት በታላቅ ተስፋና በድል እንቀበላለን።
ኢትዮጵያዊነት የድል መሰረት ነውና ለሀገራችን ከፍታ ሁላችንም በአንድነት ቆመን አዲሱን ዓመት በታላቅ ድምቀት እንድምቀው!
በሶስና አለማየሁ
Exit mobile version