Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2018 በጀት ዓመት ከግብርና ምርት ወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከግብርና ምርት ወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል አለ ግብርና ሚኒስቴር።

የግብርና ሚኒስቴር በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ ላይ ግምገማ እያካሄደ ነው።

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ÷ በ2018 በጀት ዓመት መሬትን በድግግሞሽ በማረስ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።

በዚህም በአጠቃላይ 33 ሚሊየን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉንና ከለማው መሬት ላይም 1 ነጥብ 85 ቢሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚው ትልቅ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በወተት ከ15 ነጥብ 83 ቢሊየን ሊትር በላይ፣ በማር ከ427 ሚሊየን ቶን በላይ የተመረተ ሲሆን ÷ 11 ነጥብ 7 ቢሊየን እንቁላል ለገበያ ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴዔታዋ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ በአጠቃላይ 4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።

ከተገኘው ገቢ ውስጥ የቡና ምርት የአንበሳውን ድርሻ የያዘ የዘርፉ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በአረንጓዴ ዐሻራ በበጀት ዓመቱ እስካሁን 7 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞችን መትከል መቻሉን ጠቁመው÷ በሚሊየን የሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይም የአፈርና ውኃ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸውን አስገንዝበዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት በርካታ ሀገራት የማዳበሪያ አቅርቦት ፈተና እና እጥረት በገጠማቸው ወቅትኢትዮጵያ ቀድማ በማቀድና ዝግጅት በማድረግ በቂ ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቻሏንና ፈተናውን በብቃት መሻገሯን አስረድተዋል።

በቀጣዩ በጀት ዓመት የግብርና ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት፣ ዲጂታል ግብርናን በመተግበር የአሠራር ሥርዓቱን ማቀናጀት እና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ሥራዎችን መተግበር በትኩረት እንደሚሰራባቸው ጠቁመዋል።

በአንዷለም ተስፋዬ

Exit mobile version