Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዓለም መገናኛ ብዙኀንን ትኩረት የሳበው የኢትዮጵያ ማንሰራራት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም እይታ የኢትዮጵያ ገጽታ በሁለት ፍጹም ተቃራኒ የታሪክ ትርክቶች መካከል ተጽፏል።

በአንድ ገጽ ዘመናትን የተሻገረ የክብር፣ የጥንታዊ ስልጣኔ እና የነጻነት ባለቤትነት አለ፤ በሌላኛው ገጽ ደግሞ ራስን አለመቻል፣ ተመጽዋችነትና ድህነት የሚሉ ተቃርኖዎች ተጽፈዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የዘንድሮው የጳጉሜን ወር አምስቱ ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል ይከበራሉ፡፡ እንዴት? ኢትዮጵያ ከምንድነው ያንሰራራችው?

መልሱ በአንድ ወይም በሁለት ክስተት የሚገለጽ አይደለም፡፡ ይህ ማንሰራራት በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በሕዝብ አንድነት ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊ ለውጥ ነው። ደቂቃዎችን ወስደን ቁጥሮችን አመሳክረን እናፍታታው፡፡

ይህንን አመት የኢትዮጵያ ማንሰራራት ነው ስንል…

2018 ዓ.ም ሁለተናዊ ብልጽግና እና ከፍታን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበትና የተጠናቀቁበት ዓመት ነው።

ዳግማዊ ዓድዋ ተብሎ የሚጠቀሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ስራ የገባው በዚሁ ዓመት ነው። ግድቡ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበት እና እውቀት የተገነባ የመቻላችን ተምሳሌት ሆኗል።

ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀንም ይሄንን ሀቅ ሲመሰክሩ ነው ባጅተው የከረሙት፤ ብሉምበርግ ግድቡን ለመኖሪያ ቤቶች እና የኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦትን በመሸፈን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ተስፋ ከፍ እንደሚያደርግ ዘግቧል፡፡

ሮይተርስ ግድቡን ለሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ፍላጎትን እንደሚያሟላ መዘገቡ ይህንኑ እውነታ ያጠናክራል።

ሲኤንኤን በበኩሉ ግድቡ ከመንግሥት በጀት፣ ከቦንድ ሽያጭ እና ከዜጎች መዋጮ የተገነባ በመሆኑ ሀገራዊ አንድነትን እና የፋይናንስ ነፃነትን የሚያንፀባርቅ ፕሮጀክት እንደሆነ አትቷል።

ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና ራሱ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ታላላቅ ነገሮችን መፈጸም እንደምትችል ማሳያ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ትልቁ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ የኒውክሌር ማመንጫ ፕሮጀክት፣ እና የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ በዚህ ዓመት መጀመራቸው ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዘመናዊ መጓጓዣ እና ለግብርና ሽግግር ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት አሳይቷል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ተናጠል ውጤቶች ሳይሆኑ፣ ሀገሪቱ ወደ ራስ ገዝ የኃይል አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና እና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ስርዓት የምታደርገውን ሽግግር የሚያመላክቱ የአንድ ትልቅ ራዕይ አካላት ናቸው።

እንቀጥል….

በ2018 ዓ.ም የተመዘገቡት ስኬቶች የማንሰራራት አብሳሪዎች ናቸው። በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ ገቢ የመሰብሰብ አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር በላይ ደርሷል።

ይህ አሃዝ ከቀድሞው የ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ600 ቢሊየን ብር ወይም ከ67 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ነው፡፡
ይህ እድገት የሀገሪቱን የውስጥ አቅም በግልጽ ያሳያል። አቅም ሲያድግ ደግሞ የዜጎችን ጥያቄ የመመለስ ፍጥነትን፣ የሀገር የማድረግ አቅምን ይጨምራል፡፡

ሌላ ቁጥር እናክል፡፡ ኢትዮጵያ ዘንድሮ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ 10 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ከውጪ ንግድ አግኝታለች፡፡ ይህ መገኘቱ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ያላት ተወዳዳሪነት እያደገ ለመምጣቱ ምስክር ነው።

ይህ የገቢ እድገት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከማዘመን፣ ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት እና የወጪ ንግድ ዘርፎችን ከማበረታታት ብርቱ ጥረት የመነጨ ነው፡፡

የግብርና ምርታማነት መጨመር፣ የማዕድን ዘርፍ መነቃቃት እና የቱሪዝም ገቢ እድገት የዚህ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃት አካላት ናቸው።

አይቀሬው የኢትዮጵያ ትንሳኤ….

ከቁጥሮች እና ከፕሮጀክቶች ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ሊታይ የሚችለው በሕዝቧ መንፈስ ውስጥ ጭምር ነው። ሕዳሴ ግድብን ለመገንባት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከውስጥም ከውጭም ሆነው የገንዘብ፣ የጉልበት እና የሞራል አስተዋጽኦ ማድረጋቸው፣ ኢትዮጵያውያን የጋራ ራዕይ ሲኖራቸው ምንም እንደማይገታቸው ያስመሰከረ ማሳያ ነው።

ይህ የጋራ ተሳትፎ በራሱ የማንሰራራቱ መሠረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ ምክንያቱም ማንኛውም ብሔራዊ ማንሰራራት ከቁሳዊ ግንባታ በፊት በሕዝብ ልብ ውስጥ ስለሚጀምር ነው።

እነዚህ ሁነቶች ኢትዮጵያ ከነበረችበት የድህነት እና የጥገኝነት ምዕራፍ ወጥታ ወደ ብልጽግና ጉዞዋን በግልጽ ያበስራሉ። የተገኙት ስኬቶች ለወደፊቱ ትልቅ መዳረሻ አብነታዊ መሰረት ናቸው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ አግኝታቸው የነበሩትን ወርቃማ አጋጣሚዎች በብቃት በመጠቀም ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ እና ክብሯ እየተመለሰች መሆኗን የዘንድሮው ዓመት ስኬቶች በደማቅ ሁኔታ አሳይተዋል።

የነገው ኢትዮጵያ ተስፋ በዛሬው ትውልድ ጥረት ላይ የተመሠረተ ነው።

በአፈወርቅ እያዩ

Exit mobile version