አዲስ አበባ – ነሐሴ 28፣ 2018 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ዲጂታል 2030ን በተሳካ መልኩ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ።
ሀገራዊ እና ክልላዊ የዲጂታላይዜሽን ግቦችን ለማሳካት የሚያግዝ “ኤሌክትሮኒክስ ለዲጂታል 2030 መሠረት” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአውደ ርዕዩ ተገኝተዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው እንደገለጹት፤ የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ በክልሉ ዲጂታል 2030ን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማሳየትና ማስተዋወቅ ነው።
አውደ ርዕዩ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የፈጠራ ሥራዎቻቸውንና የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ለሕዝብና ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡበት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እና የተቋማትን የዕድገት ጉዞ አስመልክቶ የፓናል ውይይቶች እንደሚደረጉ ይጠበቃል።
በአውደ ርዕዩ በተለያዩ ተቋማት የለሙ 35 የተለያዩ ዲጂታል ሥርዓቶች በይፋ ተመርቀዋል።
የተመረቁት አዳዲስ ዲጂታል ሥርዓቶችም ተቋማዊ አሰራሮችን በማዘመን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ታምኖባቸዋል።

