አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ ቀናት በዘመን ቀመር ላይ ብቻ የሚቆጠሩ አይደሉም። ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገሩ ሕልሞች፣ ለዓመታት የተነሰቁ ተስፋዎች፣ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የጸኑ ምኞቶች እውን የሚሆኑባቸው ቀናት ናቸው።
ይህ ዓመት እና በአጠቃላይም የለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ በትውልዶች የጠበቁ የተናፈቁ ተስፋ እና ምኞቶች ሆነው ተሳክተው የታየበት ዓመት ነው።
የማይቻል የተባለው ሲቻል፣ ሕልም የተባለው ወደ እውነት ሲቀየር፣ ችግር የተባለው ወደ እድል ሲለወጥ፣ አንድ ሀገር የራሷን ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ስትጽፍ ዓመቱ አሳይቷል።
የሕዳሴው ብስራት ለዓመታት የተጠበቀ፣ በተስፋና በፈተና መካከል ያለፈ፣ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ልብ ያስተሳሰረ ታላቅ ሕልም – የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ።
ግድቡ ብዙዎች ጥያቄ ያነሱበት፣ አንዳንዶች ስኬቱን የተጠራጠሩበት፣ ሌሎች ደግሞ እንዳይጠናቀቅ የተመኙበት ፕሮጀክት ለመጠናቀቅ ብስራት ደረሰ። ይህ የኮንክሪት ግድብ ብቻ አይደለም። የሕዝብ ቁርጠኝነት ምልክት ነው። የሀገር አቅም ማሳያ ነው። የትውልድ ተስፋ ምስክር ነው። ይህ ቀን ይናፈቅ ነበር!
ከረሀብ ሥጋት ወደ ስንዴ ራስን መቻል ኢትዮጵያ ለዘመናት በምግብ እጥረት የምትጠቀስበትን ታሪክ ለመቀየር ተሰራ። በግብርና ማሻሻያ፣ በመስኖ ልማት፣ በዘመናዊ አመራረትና በሰፊ የስንዴ ልማት አዲስ ታሪክ እየተጻፈ ነው።
ለምግብ ዋስትናዋ ስንዴን ከውጭ ትጠብቅ የነበረች ሀገር፣ ዛሬ የራሷን አቅም ለመገንባትና በስንዴ ምርት ራሷን ለመቻል የተጓዘችበት መንገድ የለውጥ ምልክት ሆኗል። በጠራ ራዕይ እና እቅድ ተግታ ስንዴ ከውጭ ማስገባትን ታሪክ አድርጋለች። ይህ ቀን ይናፈቅ ነበር!
ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሰላምና በማኅበራዊ ጉዳዮች ያሏትን ችግሮች ከራሷ እውነታ በመነሳት ትፍታ የሚለው የዓመታት ሕልም ነው። ስለዚህ ሀገራዊ ጉዳዮችን በሀገራዊ ዕይታ፣ በሀገራዊ ውይይትና በሀገራዊ መፍትሔ ማየት የለውጡ ዋና ዋና የፖለቲካዊ እሳቤ መሰረቶች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ውይይትና ውሳኔ መወሰንን በሀገራዊ ምክክር እውን አደረጉ። ይህ የምክክር ዘመን ይናፈቅ እና ይጠየቅ ነበር።
በከተሞች ገጽታ የሀገር የእድገት ፍጥነት ይታያል። በከተሞች ጥራት የዜጎች የሕይወት ጥራት ይመዘናል። ዛሬ በኮሪደር ልማት የከተሞች ገጽታ እየተቀየረ ነው። መንገዶች እየሰፉ፣ ለእግረኞች ቦታዎች እየተፈጠሩ፣ አረንጓዴ ስፍራዎች እየበዙ፣ የንግድና የመዝናኛ ማዕከላት እየተስፋፉ ነው።
ይህ ውበት ብቻ አይደለም ኢኮኖሚን የሚያነቃቃ፣ ቱሪዝምን የሚያሳድግ፣ ሥራ ዕድል የሚፈጥር እና የዜጎችን የከተማ ሕይወት የሚያሻሽል አዲስ የልማት አቅጣጫ ነው። ኢትዮጵያዊው ዜጋ በውብ፣ በጽዱና በዘመናዊ ከተማዎች በኩራት የሚኖርበት ቀን ይናፈቅ ነበር። ይህም በከተማ እና በገጠር ኮሪደር ተሳካ።
የጉባ ብስራቶች፤ ጉባ ዛሬ የአንድ ፕሮጀክት ስም ብቻ አይደለም። የታላቅ ሽግግር ምልክት እና የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት የመቀየር ትልቅ ራዕይ መገለጫ ነው።
ከጉባ የሚወጡ ብስራቶች የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆኑ የሀገር አቅም፣ የኢነርጂ ሕልምና የልማት ጉዞ አካል ናቸው። ከትናንት የተወረሰውን ፈተና ወደ ነገ ዕድል የመቀየር መንፈስ በዚህ ጉዞ ውስጥ ይታያል። ይህ ቀን ይናፈቅ ነበር።
ኢትዮጵያ የራሷን ታሪክ በራሷ እጅ ስትጽፍ ለማየት… ይህ ቀን ይናፈቅ ነበር!
ያ የተናፈቀ፣ የተጠበቀ ቀን በብዙ ስኬቶች ታየ!

