አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ፈጣን የከተሞች እድገትና የሕዝብ ቁጥር እድገት ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
ዘግሎባል ኢኮኖሚ የተሰኘው የመረጃ አጠናቃሪ ተቋም ÷ ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ የከተማ ሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ካላቸው ሀገራት ውስጥ በ11ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
ፈጣን የከተማ ሕዝብ ቁጥር ደግሞ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እና የመሰረተ ልማት ፍላጎት እንዲኖር ያደርጋል። ለዚህም በመደመር መንግሥት እሳቤ የሕዝቡን የቤት ፍላጎት ለማሟላትና የከተሞችን እድገት ለማፋጠን ሰፊ የልማት እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
መንግሥት በከተሞች የሚታየውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል።
የግል ባለሃብቶች በቤት ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ የሕዝብና የግል አጋርነትን የሚያጠናክሩ ርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባበሰሩበት ንግግር ሰባቱን የጉባ ብስራቶች ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ መሰረትም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ከሚደረጉ ሰባቱ ግዙፍና ስትራቴጂካዊ የሜጋ ፕሮጀክት ዕቅዶች መካከል የቤት ልማት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡
በወቅቱ መንግሥት በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ያለመ ትልቅ መርሐ ግብር ይፋ አድርጓል፡፡
ሆኖም በዘርፉ የሚስተዋለው የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ለቤት ልማት የሚሆን የረጅም ጊዜ የብድር አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖር በኢትዮጵያ እንደ ትልቅ ተግዳሮት ይጠቀሳል፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ በሀገራችን የመጀመሪያውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለውን ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ስምምነት የፈረሙት፡፡
በ100 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመውና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ደግሞ 200 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ አስተዋፅኦ የሚያደርግበት ይህ ተቋም÷ በባንክ ዘርፍ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠንን የሚቀርፍ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስን የሚያስገኝ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ “ይህ አጋርነት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡና የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ እንዲሁም በፋይናንስ ሥርዓታችን ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማስፋት ያስቀመጥነውን ግብ የሚያሳካ ወሳኝ ርምጃ ነው” ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ይህ አዲስ ተቋም የቤት ልማት ዘርፉን ሊያሻግር የሚችል ትልቅ እመርታ ሲሆን÷ መንግሥት የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለማሟላት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ወሳኝ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ስምምነቱ በተለይም በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

