አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ለአዲስ ዓመት እና ሌሎች በዓላት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ፡፡
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዎቴ ተሼ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ በመጪዎቹ የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል እና ሌሎች በዓላት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም የህብረት ሥራ ማህበራትን አቅም የማሳደግ እና በስድስቱም የከተማ አስተዳደሮች ላይ የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የምርት አቅርቦትን በተለይም ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ የዘይት፣ የስንዴ፣ የሽንኩርት፣ የቁም እንስሳት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል እና ሌሎች አቅርቦቶች በስፋት እንዲኖሩ ለማስቻል በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ምክክር መደረጉንና ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
የግብርና ምርቶችን የሚሸጡ የጅምላ አከፋፋዮች፣ አቅራቢዎች እና ቸርቻሪዎች በበቂ ሁኔታ ምርት እንዲይዙ እንዲሁም የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት አቅማቸውን አጎልብተው በበቂ ሁኔታ ምርት እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በመደበኛ ገበያዎች እና በ123 የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች ላይ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ብሎም የመገበያያ ዋጋ የዕለት ፍጆታ እቃዎች ዋጋ የመግዛት አቅምን ያገናዘበ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልምድ በመውሰድ በሀዋሳ ከተማ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራትን ለማበረታታት እና አቅማቸውን ለማሳደግ የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሸማቾች ለመጪዎቹ በዓላት በቂ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎቸ አቅርቦት መኖሩን በመገንዘብ ተረጋግተው እንዲገዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል መጪዎቹን በዓላት ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርት በሚደብቁ አካላት ላይ አስፈላጊው ርምጃ እንደሚወሰድ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

