Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

2018 እንዴት አለፈ?

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለመጠናቀቅ የቀናቶች ዕድሜ ብቻ የቀሩት የ2018 ዓ.ም ጉዞ በተለያዩ ዘርፎች የተለየ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

ዓመቱ በብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በመተግበር፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ተቋማዊ መደላድሎችን በማጠናከር ሁለንተናዊ እመርታ የተመዘገበበት ታሪካዊ ዓመት ሆኖ አልፏል።

በዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ኩነቶችን በወፍ በረር እንመልከት፦

2018 የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተበሰረበትና ዓመቱ በድል ዜና የተጀመረበት ነበር፡፡

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ የሀገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም ወደ በማሳደግ የቀጣናው የኤሌክትሪክ ማዕከል እንድትሆን አስችሏል። ይህም ኃይል ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ 477 ሚሊየን ዶላር ገቢ አስግኝቷል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም የተጀመረው በዚሁ በ2018 ዓመት ነበር፡፡

በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችለው የዚህ ሜጋ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመር የኢትዮጵያን የአቪዬሽን መሪነት የበለጠ የሚያጸና ርምጃ ነው፤ በዘርፉ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም ግዙፍ የአቪየሽን ማዕከል ለመሆን ያስችላል፡፡

ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የተከናወነውም በዚሁ ታሪካዊ ዓመት ላይ ነው፡፡

ዘመናትን የተሻገሩ የፖለቲካና የማህበራዊ ክፍተቶችን ለመድፈን የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ 4 ሺህ ተመካካሪዎችን በማሳተፍ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጠናቀቁ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫም በ2018 ከተከናወኑ ግዙፍ ሀገራዊ ሁነቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።

2018 በዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ስኬቶች የተመዘገቡበት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል መሆኗ፣ የቀይ ባሕር በርና የፍትሐዊ ወደብ ባለቤትነት ጥያቄዋን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ አጠናክራ ማስቀጠሏ፣ እንዲሁም የቀታናዊ ትስስር መሪነቷን ማረጋገጧ የዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን ከፍ አድርጎታል።

ከዚህ ባሻገር የኮፕ 32 አዘጋጅ እንድትሆን የተመረጠችበት እና በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ተሳትፋ የአፍሪካን አጀንዳዎች ያንጸባረቀችበት ዓመት ነበር፡፡

የገበያ መር የምንዛሬ ሥርዓት:- በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ የተተገበሩት የፖሊሲ ለውጦች የማክሮ ኢኮኖሚውን ያረጋጉ ሲሆን፣ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መተግበሩ የኢመደበኛ ገበያውን ልዩነት በማጥበብ የውጭ ንግድ ገቢ እንዲያድግ አድርጓል።

የማዕድን ዘርፍ ትንሣኤ ያሳየበት ዓመት ነበር፡፡ የማዕድን ዘርፍ የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻውን ወደ 1 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል። የወርቅ ኤክስፖርት ገቢም ከ3 ነጥብ 48 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱ፣ እንዲሁም የድንጋይ ከሰልና የኖራ ድንጋይ በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸው በቢሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ለማዳን አስችሏል።

የሰብልና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፦ በዓመቱ 33 ሚሊየን ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ ሰብሎች ተሸፍኖ 1 ነጥብ 85 ቢሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

የሌማት ትሩፋት እና ኤክስፖርት፦ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከ15 ነጥብ 83 ቢሊየን ሊትር በላይ ወተት እና 11 ነጥብ 7 ቢሊየን እንቁላል ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ከግብርና ወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተግኝቷል። የኢትዮጵያ ቡና የምንጊዜም ከፍተኛውን የኤክስፖርት መጠን አስመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፡ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘጋጅተው የነበሩ 917 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ፦ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና የካፒታል ገበያን በማስጀመር የፋይናንስ ሥርዓቱን አነቃቅቷል።

የቱሪዝም ዘርፍ እድገት፡ የታደሱ ቅርሶች፣ የኮሪደር ልማትና የገበታ ፕሮጀክቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ገቢ አስግኝተዋል።

በጤና ዘርፍ እንደ ማርበርግ ያሉ ድንገተኛ ወረርሽኝ በጽናትና በሙያዊ ብቃት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ልማትና በተቋማዊ ግንባታ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ወደ ላቀ የብልጽግና ከፍታ ጉዞዋ ላይ እንደምትገኝ ያረጋገጡ ናቸው።

በአጠቃላይ 2018 ዓ.ም በፈተናዎች ውስጥ አስደናቂ ሀገራ ስኬቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነበር።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version