አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜጎች የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የመንግሥትና የሕዝብን አስተዳደራዊ ግንኙነት ያጠናክራል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የክልሉን ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምዝገባ ሲስተም የሚያስተዋውቅ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ፥ የዜጎች መረጃ ዘላቂነትና ታማኝነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተደራጀ የምዝገባ ሥርዓት ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የምዝገባ ስርአት ጊዜን፣ ጉልበትንና ወጪን እንደሚቆጥብና የልማት ስራዎችን በተጨባጭ መረጃ ላይ መሰረት አድርጎ ለመስራት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በመሆኑም ከአገልግሎቱ የሚገኘው መረጃ የስራ ቅልጥፍናንና የህዝብን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለላቀ ውጤታማነት ሁሉም ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ኃላፊ መዓዛ በዛብህ በበኩላቸው ፥ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽ መደረጉ ፈጣንና ደህንነቱ የተረጋገጠ ትክክለኛ መረጃን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ761 የምዝገባ ጣቢያዎች ከአንድ ሚሊየን በላይ ኩነቶች ተመዝግበዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።

