አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምስራቅ አፍሪካ ብርሃን ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባለፈው በጀት ዓመት ሀገሪቱ 9 ነጥብ 73 ጊጋ ዋት ኃይል አመንጭታለች፡፡
ለጎረቤት ሀገራት ከኤሌክትሪክ ሽያጭ የተገኘው ገቢም 475 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ እድገት ያሳያል።
በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፤ ጎረቤት ሀገራት የወደፊት ኢኮኖሚያቸውን ከኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል መረብ ጋር በስፋት እያስተሳሰሩ ይገኛሉ።
ይህ እውነታ ራሱ ግድቡን ከሀገራዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክትነት አልፎ የቀጣናዊ ትስስር ማዕከል እንዲሆን አድርጎታል።
ኬንያ ኃይል ለመግዛት ፍላጎቷን በኢትዮጵያ ብርሃን እያሟላች ነው፤ ደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ ተጨማሪ የግዥ ስምምነት ለመፈራረም ማቀዷን ገልጻለች፤ ጅቡቲ ተመሳሳይ ነባሩን የኤሌክትሪክ ትስስር በማጠናከር ላይ ትገኛለች።
ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ኃይል ገዢ ከሆኑ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትስስር ትርጉሙ ጥልቅ ነው፤ ይህም ከዓባይ ውሃ የሚጠጡ ሀገራት ከንግድ ልውውጥ ባሻገር በጋራ መሠረተ ልማት ላይ የተመሠረተ መተማመንና መደጋገፍ እንዲገነቡ ያደርጋቸዋል።
ኃይል ማምረትና መሸጥ ብቻውን ግብ ሳይሆን፤ ለጋራ ብልጽግና መሠረት ነው፤ ኬንያ ግድቡን እንደ መተማመንና ትስስር መገንቢያ መሠረት ትመለከተዋለች።
ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ በግድቡ ምረቃ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “የአፍሪካ የራስ አቅም ልማት ማሳያና የአህጉራዊ ኃይል ትስስር ራዕይ አካል ነው” ማለታቸውም ይሄንኑ የሚያጠናክር ነው።
በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ አጽንኦት እንደተሰጠው፤ የኃይል ትስስር ራሱ የፖለቲካ መተማመንን የሚያጠናክር መሣሪያ እየሆነ መጥቷል ማለት ነው።
ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የሚነሳው የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ከተሞቿ፣ መንደሮቿ፣ ትምህርት ቤቶቿና ጤና ተቋማቷ መድረሱ ለዜጎቿ አዲስ የእድገት እድል እንደሚፈጥር ገልጻለች፡፡
ይህም የኢትዮጵያ እድገት የሁሉም ሀገራት ብልፅግና አካል ተደርጎ የሚታይበትን አዲስ የቀጣናዊ አስተሳሰብ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ትብብርን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ማዕከል አድርጋ ትቀጥላለች።
ሚኒስትሩ በለንደን ቻተም ሃውስ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር፤ የዓባይ ወንዝ ጉዳይ በሉዓላዊነት፣ በራስ አቅም መተማመንና በሌሎች ላይ ጉዳት ሳያደርሱ የመልማት መብት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
«ልማትን እንደ ስጋት የሚቀርጹ አካሄዶችን አንቀበልም» ነበር ያሉት።
ኢትዮጵያ በኢጋድ ቀጣና ያላትን ስትራቴጂያዊ ኃላፊነት አጠናክራ እንደምትወጣ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥም ካሉ ሀገራት ጋር ተባብራ ወንዙ ለሁሉም ተፋሰስ ሀገራት የብልጽግና እና የወዳጅነት ምንጭ እንዲሆን እንደምትሠራ አቋሟን ደጋግማ አሳይታለች።
ይህ አቋም የቀጣናውን መረጋጋት ጊዜ ካለፈባቸውና ብቸኝነትን ከሚሹ የይገባኛል ጥያቄዎች ባለፈ በትብብርና በእኩልነት መርህ ላይ መገንባት እንዳለበት የሚያሳይ ነው።
በአፈወርቅ እያዩ

