አዲስ አበባ፣ነሐሴ 30፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ያለፉት አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ዓመታት ነበሩ። በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታየው ለውጥ አበረታች እና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያም ያለፉትን 5 ዓመታት የሰራቻቸው በቁጥር የተመዘገቡ ስኬቶች ለቀጣዮቹ 5 ዓመታት የሚሆኗትን ስንቆች የቋጠረችባቸው ናቸው።
ኢትዮጵያም ከድህነት ለመውጣት እና ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት ከሀገራቸው አልፈው ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ እድገት እንዲያስመዘግቡ ትሻለች፡፡
ለዚህ የሚያግዝ ተግባርንም እያከናወነች ትገኛለች። ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ብቻ ታስበው ይገነቡ የነበሩትን የኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶች በሀገር ውስጥ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ይሰሩ የነበሩ አምራቾች ገብተው እንዲሰሩባቸው እየተደረገ ነው፡፡
የገላን ጉራ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ሲሆን፤ ፓርኩ ውስጥ ገብተው እየሰሩ ያሉት ወጣቶች ከአራት እና አምስት ዓመታት በፊት በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው እየሰሩ የነበሩ ናቸው።
አሁን ላይ ወጣቶቹ ለሌሎች የስራ ዕድል በመፍጠር ሰራተኞችን ቀጥረው ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ እያሰሩ ይገኛሉ።
እንዲህ አይነት የሚሰሩ እጆችን የምታበረታታው ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን ለማዘመን አጋዥ የሆኑ መሳሪያዎችን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በሀገር ውሰጥ ሙሉ በሙሉ የማታመርትበት ምክንያት አይኖርም፡፡
ከዚህ ቀደም ያልተጣራ ወርቅን ለዓለም ገበያ ታቀርብ የነበረችዉ ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የራሷን የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ ከፍታለች።
ታዲያ ይህ ፋብሪካ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያን የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግም ይጠበቃል።
የዓለም ተለዋዋጭ የጂኦፖለቲካ ምህዳር የሚፈትነውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለማቃለል እና በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራች ያለችው ስራ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአርሶ አደሮቿን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እና የዋጋ ውድነቱን ይፈታል።
አይን አይቶ ልብ ይፈርዳል እንዲሉ ኢትዮጵያ የኢንድስትሪ ዘርፏን አሳድጋ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶቿን አስፍታና የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን አሟልታ የዜጎቿን ህይወት ለውጣ እንኳንም ያኔ ጀመርኩ የምትልበት ወቅት ላይ ናት፡፡
በእመቤት ሲሳይ

