Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያና አፋር ክልሎች በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ አጋጠመ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች በአዋሽ ተፋሰስ በሚገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
 
በኦሮሚያ ክልል እና በአፋር ክልሎች በቅርብ ሳምንታት በተከሰቱ ጎርፎች በርካቶች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።
 
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳዋ ኢሉ ወረዳ፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፊል ኤጄሬ ወረዳ፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ቦራ፣ አዳማ፣ ከፊል ፈንታሌ ወረዳዎች እና መተሃራ ከተማ የጎርፍ አደጋው አጋጥሟል።
 
በተመሳሳይ በአፋር ክልል አሚበራ ወረዳ፣ አሳኢታ፣ ዱብቲ፣ ገለአሉ፣ ገዋኔ እና አፋምቦ ወረዳዎች የገርፍ አደጋ ማጋጠሙን የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበጀ መንገሻ ለፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል።
 
በአካባቢዎቹ የጎርፍ አደጋው ከመከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል በበጋ ወራት የወንዙን የመሸከም አቅም የማስፋት ስራዎች እና የጎርፍ መከላከያ ግንባታዎች መከናወናቸው ነው የተነገረው።
 
በክረምቱ ወቅትም በሰው ሃይል ጭምር የመከላከል ስራ ሲሰራ ቢቆይም የክረምቱ ዝናብ ክብደት እያየለ በመምጣቱ እና የግድቦች የውሃ ሙሌት ከአቅም በላይ መሆኑን ተከትሎ በተፋሰሱ በሚገኙ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ መሆኑ ተነግሯል።
 
በዛሬው ዕለት ካጋጠመው የጎርፍ አደጋ ለሚወጡ የህብተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ሀላፊው ገልፀዋል።
 
የጎርፍ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በቅድሚያ የሰው ህይወት የማዳን ስራ ከክልሎች ብሎ ከዞን እና ወረዳ አመራሮች ጋር እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል።
 
የክረምቱ የዝናብ ክብደት አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሜቴዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የገለፁት ሃላፊው አቶ አበጀ መንገሻ በአዋሽ ወንዝ ገባሮች እና በዋናው በአዋሽ ወንዝ የሚገኙ ዜጎችን ከአካባቢዎቹ ማውጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
በጎርፍ ምክንያት ከአካባቢዎቹ ለተፈናቀሉ ዜጎችም የክልል መንግስታት እና የፌዴራል መንግስታት ድጋፍ እያረጉ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ለኮሮና ቫይረስ እዳይጋለጡም በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
 
በዘላቁነትም ችግሩን ለመቅረፍ በአካባቢው የሚከሰተውን ጎርፍ አደጋ መከላከል እንዲቻል በአዋሽ ተፋሰስ ልማት ፅህፈት ቤት የተሰሩ ጥናቶችን ወደ ተግባራ መቀየሩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
Exit mobile version