አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ ሥራዎቹ ባሻገር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው አሉ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ለ “ስለ እናት” በጎ አድራጎት ድርጅት የ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና ለውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን በጎ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ተቋሙ “በበጎነት” በሚል ስያሜ በቀረጸው ልዩ መርሐ ግብር በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 50 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከ75 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በእነዚህ ተቋማት ሥር ለሚገኙ 22 ሺህ 212 አረጋውያን፣ ሕጻናት፣ እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞች የዕለት ተዕለት ሕይወት መሻሻል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ማኅበራዊ ግዴታውን ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የፈጸመ ሲሆን፣ የዘንድሮውን ጨምሮ እስካሁን ከ117 በላይ ለሚሆኑ የበጎ አድራጎት ተቋማት ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
ኩባንያው የነገ የሀገር ተረካቢ ትውልዶችን ለመደገፍ ትምህርትን መሠረት አድርጎ፣ “ለነገ ተስፋዎች” በተሰኘው መርሐ ግብሩ ሰፊ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም በመላው ኢትዮጵያ አነስተኛ ገቢ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለተወጣጡ 105 ሺህ 496 የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ ከ113 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የመማሪያ ደብተሮችን ማበርከቱ ተጠቁሟል፡፡

