አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የአካባቢውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ መጠቀም ተችሏል አለ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ።
የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስሕቦችን በመለየት እና በማልማት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ማሳደግ ተችሏል፡፡
ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ የመሰረት ልማት እና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ላይ በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
በዚህም የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን የመለየት ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ቀድመው የለሙት ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም ያልለሙትን ደግሞ በማልማት የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስት ፍስት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊን በላይ ዜጎች ክልሉን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ ከዘርፉ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡
በየአካባቢው ያሉ መስህቦችን የማልማት እና መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የክልሉ የቱሪዝም እንቀስቃሴ ዕድገት በየዓመቱ 14 በመቶ ዕድገት እያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የከተማ ቱሪዝም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰሩ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከውበት ባለፈ የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማሳደግ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ በመስከረም ወር በርካታ በዓላት እንደሚከበሩ የገለጹት የቢሮው ኃላፊ ለአብነትም የሀዲያ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ያሆዴ፣ የመስቀል በዓል በጉራጌ፣ በከምባታ፣ ጠምባሮ እና ዶንጋ የሚከበረው የመሰላ በዓል እንዲሁም የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ሄቦ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በእነዚህ በዓላት ላይ ከክልሉ ተወላጆች በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ እንግዶች እንደሚመጡ ጠቁመው፤ ለበዓላት የሚመጡት እንግዶች በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል፡፡
ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የሚመጡት እንግዶች የቱሪዝም መስህቦችን እንዲጎበኙ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም አንስተው፤ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲመለከቱም እድል እየተፈጠረ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስሕቦችን በማሻሻል እና መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

