Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የለውጡ ዘመን የትውልድና የሀገር አቅጣጫ የተወሰነበት የእመርታ መሰረት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የለውጡ ዘመን የትውልድና የሀገር አቅጣጫ የተወሰነበት የእመርታ መሰረት ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ሚኒስቴር በተካሄደው የእመርታ ቀን አከባበር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዕለቱ ኢትዮጵያ ከፈተና ወደ ዕድል፣ ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል፣ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረች ያለችበትን ታሪካዊ ምዕራፍ የምናበስርበት ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመመራት የተካሄዱ ሪፎርሞች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መሰረት ማጠናከራቸውን ተናግረዋል።

በምግብ ሉዓላዊነት ዘርፍ አኩሪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በመስኖ ስንዴ፣ በሩዝ፣ በበቆሎና በሌሎች ሰብሎች ልማት የተገኙ ስኬቶች በብርታታችን ያጨድናቸው የትጋታችን አዝመራዎች ናቸው ብለዋል።

ፈጠራ እና ፍጥነት እሴቶቹ የሆኑት የመደመር መንግሥት የጀመራቸው የሌማት ትሩፋት ፍሬዎች፣ የክላስተር እርሻና የዘመናዊ ግብርና አሰራሮች ተግባራዊነት ኢትዮጵያ የራሷን ምግብ የማምረት አቅሟን አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

የምግብ ሉዓላዊነት ለእኛ የልማት ግብ ብቻ ሳይሆኑ፤ የነፃነታችን፣ የክብራችንና የፅናታችን ማረጋገጫ ደማቅ የትውልዳችን ማህተም ጭምር ናቸው በማለት አውስተዋል፡፡

በተጨማሪም በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን በቱሪዝምና በዲጂታል ዘርፎች የተሰራው የፖሊሲና የአመራር ለውጥ የኢትዮጵያን አዲስ አሻጋሪ ምዕራፍ መክፈታቸውን ጠቅሰዋል።

የመደመር መንግሥት በጀመራቸው ዘርፎች ሁሉ የታየው የዛሬው እመርታችን የትናንት ቁርጠኝነታችን ፍሬ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፍታችንም የዛሬ ትጋት ውጤት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የመደመርን ጎዳና በመተለም፤ እያመረተች፣ እየተለወጠችና እያንሠራራች ነው ብለዋል፡፡

ይህንን የእመርታ ቀን የስኬቶቻችን ማሳያ ብቻ ሳይሆን፤ ወደሚቀጥለው ከፍተኛ የዕድገት ማዕረግ ለመሸጋገር የጋራ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ዕለት ልናደርገው ይገባል ብለዋል።

በለይኩን አለም

Exit mobile version