አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (ኦሲሲ) በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከ17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል፡፡
የተቋሙ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 ዓ.ም የሥራ ዕቅድ ውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸናፊ ዳባ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የታቀዱ ሥራዎችን በስኬት ለማከናወን የተተገበረው ዲጂታል ሥርዓት ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል፡፡
በተለይም በአስፋልት መንገድ፣ በመጠጥ ውሃ፣ በመስኖ ግድብ፣ በሕንጻ፣ በስታዲየም፣ በውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከ17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
አፈጻጸሙ ከ2017 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ እድገት አሳይቷል ያሉት ኃላፊው ÷ በፕሮጀክቶችና ትላልቅ ማሽኖች ላይ የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ በመትከል የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱ ለስኬቱ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
የኮርፖሬሽን ስትራቴጂክ ዕቅድና ቢዝነስ ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ ኢሬና በበኩላቸው ÷ በዓመቱ በቅንጅት በተከናወኑ ሥራዎች ለረጅም ዓመታት ሲጓተቱ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም የአርጆ ዲዴሣ ግድብ፣ የሆሚቾ አስፋልት መንገድ፣ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና የተለያዩ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ጠቅሰዋል፡፡
ከ51 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው ÷ በቀጣዩ ዓመት የተያዘውን እቅድ ለማሳከት በቁርጠኝነትና በትብብር እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
የግምገማ መድረኩ ተሳታፊዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ መርሐ ግብር ማካሄዳቸውንም የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመልክቷል፡፡
የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ከ17 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ

