አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጨምሮ ሰፋፊ የልማት ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡
ከእነዚህ የግብርና ልማት ተነሳሽነቶች መካከል ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የቻለችና የበለፀገች ሀገር የማድረግ ትልቅ ርዕይን አንግቦ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ ይጠቀሳል፡፡
መርሐ ግብሩ በተለይም በስጋና በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮና ማር ምርት እንዲሁም ማርባት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ አጠቃላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን አመጋገብ ለማሻሻል ያለመ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም የሌማት ትሩፋት የልማት ዘመቻን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ መርሐ ግብሩ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
በቂ እና አመርቂ ምግብ ለማግኘት የሚያስችል፤ በአጠቃላይ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑንም አንስተው ነበር፡፡
የሌማት ትሩፋት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዘርፉ አበረታችና ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል።
የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያን እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት ህክምና አገልግሎትን በማስፋፋትና የከብት መኖ አቅርቦትን በማሳደግ የወተት ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ተደርጓል።
እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ፤ የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ወዲህ በመጀመሪያው ዓመት የወተት ምርትን 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከእጥፍ በላይ በማደግ ወደ 15 ነጥብ 8 ቢሊየን ሊትር ከፍ ብሏል፡፡
ይህም ለአነስተኛ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኗል።
በአጭር ጊዜና በትንሽ ቦታ የዶሮ እርባታን በመደገፍ በሚሊየን የሚቆጠሩ የዶሮ ጫጩቶች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል።
ይህም በየጓሮው የሚካሄድ እርባታን በማስፋፋት የእንቁላልና የዶሮ ስጋ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል።
በዶሮ እርባታ 26 ሚሊየን የነበረው የጫጩት ሥርጭት ወደ 184 ሚሊየን ከፍ ያለ ሲሆን፤ የዓሳ ምርት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረበት 78 ሺህ ቶን ወደ 307 ሺህ ቶን ማድረስ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ለማር ምርት ያላትን ተፈጥሯዊ ፀጋ በመጠቀም ዘመናዊ የቀፎ ቴክኖሎጂዎችን እና ስልጠናዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የማርና ሰም ምርት ጥራትና መጠን እንዲያድግ ተደርጓል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በዚሁ መርሐ ግብር አማካኝነት 428 ሺህ ቶን የማር ምርት የተገኘ ሲሆን፤ ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለወጪ ንግድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ የታለሙ ስራዎች ውጤት በማሳየት አርሶ አደሮችና የከተማ ወጣቶች በእንስሳት ማደለብ ስራ ላይ በመሰማራት የአገር ውስጥ የስጋ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ማዘጋጀት ችለዋል።
በዚህም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በመደገፍ፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘውን የእመርታ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥንባቸው ይገኛሉ ካሏቸው የልማት ሥራዎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ

