Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የክልሉ እንስሳት ልማት ሃብት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አሰፋ ፎና ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡

በመርሐ ግብሩ የወተት፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ዓሣ እና ማር ምርታማነት ላይ ከፍተኛ እድገት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በወተት ሃብት ላይ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው ÷ በተለይም ዝርያ የማሻሻል ሥራ ላይ በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የዝርያ ማሻሻያ ሥራው 6 ነጥብ 5 በመቶ ነበር፤ አሁን ላይ ግን የዝርያ ማሻሻያ ሥራው ወደ 21 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን ነው ያስረዱት፡፡

በመርሐ ግብሩ በክልሉ ያለው የወተት ሃብት ከቤተሰብ አልፎ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመው ÷ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በላይ ወተት ለኢንዱስትሪ ግብዓት መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር መተግበር ከጀመረ ወዲህ የዶሮ እና እንቁላል ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አመልክተዋል፡፡

ከመርሐ ግብሩ በፊት ከ1 ሚሊየን በታች የእንቁላል ጣይ እና የስጋ ዶሮ ይሰራጭ እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 20 ሚሊየን የእንቁላል ጣይ እና የስጋ ዶሮ መሰራጨቱን ጠቁመዋል፡፡

በ2019 በጀት ዓመት 25 ሚሊየን ጫጩቶችን ለማሰራጨት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 600 ሚሊየን እንቁላል መሰብሰብ መቻሉንና መርሐ ግብሩ ገበያ ከማረጋጋት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የማር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ሺህ ቶን በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

የዓሳ ሃብትን ለማሳደግ ውሃ በሚገኝበት አካባቢ ሁሉ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ዝርያ የማሻሻል፣ ግብዓት የማቅረብ፣ መኖ የማዘጋጀት እና በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመርሐ ግብሩ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version