አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ጳጉሜን 2 የማንሠራራት ቀንን ምክንያት በማድረግ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ነው አለ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ፡፡
ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ግማሽ ቀን በሚቆየው አገልግሎት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች፣ የከተማ አውቶቡሶችና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለደንበኞቻቸው መልካም የአዲስ ዓመት በመመኘት ጭምር እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው እንዳሉት÷ በነጻ ትራንስፖርት አገልግሎቱ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የመዲናዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የአዲስ አበባ የማንሠራራት ማሳያ ከሆኑ ልማቶች መካከል የትራንስፖርት ዘርፉ ዋነኛው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዳኛቸው÷ የመዲናዋን ዘመናዊነት የሚመጥኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ዘርፉን ማንሠራራት ተችሏል ብለዋል።

